የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ የ17ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ሻሸመኔ ከተማ መሪነቱን ያሰፋበትን ውጤት ሲያስመዘግብ ንብ ፣ ቦዲቲ እና ነቀምትም ተጋጣሚዎቻቸውን ረተዋል።
የሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ ንብን ባለ ድል ያደረገ ውጤት ተመዝግቦበት የተጠናቀቀ ነበር። አሰልቺ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች በተበራከቱበት በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በተለይ አስራ አምስት ያህል ደቂቃዎች ተመጣጣኝ የሚመስል ፉክክሮችን ያስመለከተን ቢመስልም ከመስመር እና ከቆሙ ኳሶች ልዩነት ለመፍጠር የሚጫወቱት ንቦች 33ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ቀኝ ካደላ ቦታ ላይ ታምራት ስላስ የተገኘን የቅጣት ምት ሲያሻማ አምበሉ ንስሀ ታፈሰ በግንባር ገጭቶ አስቆጠሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል አምቦ ከተማዎች በተለይ ረጃጅም ኳስ ላይ ትኩረትን አድርገው ወደ ጨዋታ ለመመለስ ትግል ውስጥ በነበሩበት ሒደት ውስጥ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተሰጠው የጭማሪ ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ተቀይሮ እየገባ ግብን ባለፉት ጨዋታዎች ላይ እያስቆጠረ የመጣው ናትናኤል ሰለሞን በጥሩ አጨራረስ ተጨማሪ ግብን በማከል ጨዋታው በንብ የ2ለ0 አሸናፊነት ተደምድሟል።
5 ሰዓት ሲል የካፋ ቡና እና ቦዲቲ ከተማ ጨዋታ በሁለተኛ የዕለቱ መርሀግብር ቀጥሎ ተከናውኗል። ጠንካራ ፉክክር እና ማራኪ የኳስ ፍሰት ያሳየን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መሀል ሜዳ ላይ ያመዘኑ እንቅስቃሴዎች ተበራክተውበት እና የሚገኙ ኳሶችን ግን ወደ ጎልነት ከመለወጥ አንፃር እምብዛም የሆነበት ነበር ማለት ይቻላል። ጨዋታው በተጀመረ ገና አራተኛው ደቂቃ ላይ አስጨናቂ ሉቃስ ግልፅ ዕድልን አግኝቶ መጠቀም ያልቻለበት አጋጣሚ ምናልባትም ካፋን መሪ አድርጋ መነቃቃት የምትፈጥርላቸው አጋጣሚ ብትሆን ከዚህች ኳስ ማባከን በኋላ ቦዲቲዎች የጨዋታ መንገዳቸውን ወደ መስመር በመለወጥ በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል።
ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል በመድረሱ የተዋጣላቸው እና ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ችግሮች በቀዳሚው አጋማሽ ይንፀባረቅባቸው የነበሩት ቦዲቲዎች 71ኛው ደቂቃ ላይ የመስመር አጥቂው አማኑኤል አሊሳ ግብ አስቆጥሮ ቦዲቲ ከተማ 1-0 አሸንፎ በድል ጨዋታው ተወጥቷል።
የሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን እና ነቀምት ከተማ ጨዋታ ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክርን ያስመለከተን ሆኖ ተጠናቋል። ሁለት መልክ የነበረውን ሁለት አጋማሾችን ያሳየን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የነቀምትን ተሻጋሪ እና ፈጣን የሽግግር አጨዋወትን በአንፃሩ ደብረብርሃንኖች መሀል ሜዳው ላይ በይበልጥ በመቀባበል ለአጥቂዎች በማሾለክ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር የጣሩበትን መንገድ ያየንበት ሆኗል። የነቀምት ከተማ አንፃራዊ ብልጫን ያሳየን የመጀመሪያው አርባ አምስት በተመስገን ዱባ አማካኝነት ሙከራን አድርገው ከግቡ መስመር ላይ ልደቱ ጌታቸው ባወጣበት ጥቃት መሰንዘርን ጀምረዋል።
ጨዋታው 24ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ወደ ግራ ካደላ ቦታ ከቅጣት ምት የተሻገረን ኳስ ለታ ዋቅጋሪ በግንባር በመግጨት ነቀምትን መሪ ያደረገች ግብን አስገኝቷል። መሀል ሜዳ ላይ አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች የሚያሳልፉት ደብረብርሃኖች ለአጥቂዎቹ የተሻ እና መስፍን በመጣል ዕድል ለመፍጠር ሞክረው በተለይ የመስፍን ኪዳኔ ራስ ወዳድ መሆን ቡድኑ ወደ አቻነት እንዳይመጣ ያደረገ ዋነኛ ምክንያት ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ቀጥሎ ደብረብርሃን ፍፁም የጨዋታ ብልጫን ወስደው በተጋጣሚያቸው ላይ ተደጋጋሚ ጥቃትን መሰንዘር ቢችሉም ደካማው የአጨራረስ ብቃታቸው በመልሶ ማጥቃት በተጫወቱት ነቀምቶች ተጨማሪ ጎል እንዲያስተናግዱ ሆኗል። 66ኛው ደቂቃ ላይ በድንቅ አጨራረስ ለታ ዋቅጋሪ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አክሎ በ2-0 የነቀምት አሸናፊነት ጨዋታው ተቋጭቷል።
በበርካታ ተመልካቾች ፊት ታጅቦ የተደረገው የዕለቱ የማሳረጊያ ጨዋታ ሻሸመኔን ባለ ድል አድርጎ ፍፃሜውን አግኝቷል። የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ እና በርካታ የክለቡ ደጋፊዎች እንዲሁም የእንጅባራ ደጋፊም ጭምር በሜዳ ላይ ተገኝተው ክለቦቻቸውን በደገፉበት ጨዋታ እንጅባራ ከተማ በኳስ ቁጥጥሩ ፍፁም ብልጫን ወስደው የታዩበት ቢሆንም ለስህተት ተጋላጭ የነበረው የኋላ መስመሩ ለሻሸመኔዎች ተሻጋሪ እና ፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት አመቺ ሆኖላቸው ተስተውሏል። ኳስን ከአማካይ ክፍሉ በአግባቡ ምንጫቸው አድርገው እንጅባራዎች ወደ ፊት ለመሔድ ቢታትሩም ደካማ የአጥቂ ክፍላቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል። 13ኛው ደቂቃ ላይ ምትኩ ማመጫ ከቅጣት ምት አሻምቶ ያሬድ በልጉ በግንባር የገጨበት አጋጣሚ ተጠቃሿ ነች። የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ በመልሶ ማጥቃት ፉዓድ መሐመድ የትኩረት ማዕከላቸው ያደረጉት ሻሸመኔዎች ተደጋጋሚ ዕድልን ፈጥረው ተመልክተናል።
ከዕረፍት መልስ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቀጥሎ እንጅባራዎች የኳስ የበላይነቱን ወስደው ግልፅ ዕድልን ለመፍጠር የጣሩ ቢሆንም የሚሞከሩ ኳሶችን ከአጥቂዎቹ ይልቅ ግብ ጠባቂው ታምራት ዳኜ በቀላሉ የሚያወጣቸው ነበሩ። የሆነው ሆኖ 58ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ጥላሁን የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሻማችን የቅጣት ምት ልማደኛው ፉዓድ መሐመድ በቀጥታ የግብ ጠባቂ ስሆተት ታክሎበት ከመረብ አሳርፏት ጨዋታው 1ለ0 ሻሸመኔን ባለ ድል በማድረግ ተጠናቋል። ውጤቱም ሻሸመኔ ከተማን በመሪነቱ አዝልቆታል።