ሊጉ በአፍሪካ ዋንጫ ምክንያት ከመቋረጡ በፊት በነበረው የመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ዓበይት ክለብ ነክ ጉዳዮች በተከታዩ ፅሁፋችን ተዳሰዋል።
👉 ፋሲል ከነማ ዕረፍቱን በመሪነት ያሳልፋል
የሊጉ ውድድር ለአፍሪካ ዋንጫ ከመቋረጡ በፊት በነበረው የመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት መከላከያን ያስተናገደው ፋሲል ከነማ በያሬድ ባየህ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ በማሸነፍ ከተከታዩን በአንድ ነጥብ በመብለጥ በአስራ ስምንት ነጥብ ሊጉን እየመራ የሚቆይ ይሆናል።
ፋሲል ከነማዎች በኳስ ቁጥጥር ረገድ የተሻሉ በነበሩበት ጨዋታ ለግቡ ቀርቦ ይከላከል የነበረውን የመከላከያን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ለማለፍ በጣሙን ተፈትነው ተመልክተናቸዋል። ነገር ግን በሁለተኛው አጋማሽ በተወሰነ መልኩ ለቀቅ ባለ መንገድ አጋማሹን ለመቅረብ የፈለጉት መከላከያዎች ጨዋታውን ከቀደመው በተሻለ ክፍት ማድረጋቸው ለፋሲሎች ይበልጥ የተመቸ ሆኗል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በያሬድ ባየህ ፍፁም ቅጣት ምት መሪ መሆን ችለው የነበሩት ፋሲሎች በመስመሮች በኩል (በተለይ በቀኝ መስመር) በተሻለ ተደጋጋሚ ጫናዎችን መፍጠር ችለው ነበር።
የሊጉ ውድድር ወደ ሲሶው እየተጠጋ በሚገኝበት በዚህ ሰዓት ፋሲል ከነማዎች በ18 ነጥቦች ሊጉን ቢመሩም በደረጃ ሰንጠረዡ ዘጠነኛ ደረጃ እስከሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና ድረስ ካሉት ቡድኖች ጋር ስድስት እና ከዛ በታች ባነሰ የነጥብ ልዩነት መቀመጣቸው የአምናውን ክብራቸውን ለማስጠበቅ ጠንካራ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው ማሳያ ነው። በመሆኑም ቡድኑ በቀጣይ ሊጉ ከዕረፍት ሲመለስ መሪነቱን ለማስቀጠል ክፍተቶችን ባስተዋለባቸው አንዳንድ የጨዋታ መንገዶች ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግ ከተከታዮቹ ከሚደርስበት ጫና ለመላቀቅ የሚያስችል ቀጣይነት ያለው ውጤት ማስመዝገብ ይኖርበታል።
👉 ሲዳማ ቡናን የሚመስለው ሲዳማ ቡና
ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የከረመው ሲዳማ ቡና በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወላይታ ድቻን ፍፁም ከሆነ የጨዋታ የበላይነት ጋር በማሸነፍ በቡድኑ ዙርያ ያጠላውን የስጋት አየር በተወሰነ መልኩ መበተን የቻለበትን ውጤት በወሳኝ ሰዓት አስመዝግቧል።
ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ በከፍተኛ የማጥቃት ፍላጎት ጨዋታውን የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች የተከላካይ መስመራቸውን ወደ ፊት አስጠግተው እና ሁለቱን የመስመር ተከላካዮች ሙሉ የማጥቃት ነፃነት በመስጠት በተደጋጋሚ መሀል ለመሀል በሚነሱ ኳሶች ጭምር የወላይታ ድቻን ሳጥን ሲፈትኑ ውለዋል።
በጨዋታው የቡድኑ ተጫዋቾች ላይ ይታይ የነበረውን የራስ መተማመን እና የማሸነፍ ፍላጎትን ለተመለከተ ቡድኑ በውጤታማነት ግስጋሴ ላይ የሚገኝ እንጂ በውጤት ማጣት ጫና ውስጥ ያለ አይመስልም ነበር። እንደነበራቸው ብልጫ እና እንደፈጠሯቸው ዕድሎች ከ2-0 በላይ በሆነ ውጤት ማሸነፍ በተገባቸውም ነበር።
በጨዋታው እጅግ ቁልፍ በነበረው የመሀል ሜዳው ፍልሚያ ላይ በተደጋጋሚ አንድ ተጨማሪ ሰው በእንቅስቃሴ ወደ መሀል በማስገባት የቁጥር ብልጫ እያገኙ የነበሩት ሲዳማዎች በተለይ ፍሬው ሰለሞን ከአጥቂ ጀርባ ሆኖ ጨዋታውን ቢጀምርም በጥልቀት ወደ ኋላ እየተሳበ ኳሶችን የሚያሰራጭበት እንዲሁም አደገኛ ኳሶችን ወደ ፊት የሚጥልበት መንገድ የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ሲዳማ ቡናዎች እንዲያጋድል ያስገደደ ነበር።
በ2ኛ የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን 3-0 በሆነ ውጤት ከረቱ ወዲህ ማሸነፍ ተስኗቸው የሰነበቱት ሲዳማ ቡናዎች ወላይታ ድቻን ከሰባት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ በማሸነፍ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማስመዝገብ መቻላቸው ቡድኑ የዕረፍቱን ጊዜ በተሻለ መነቃቃት ውስጥ ሆኖ እንዲያሳልፍ የሚያስችል እንደሚሆን ይጠበቃል።
👉 አንገት የማያስደፋው የአዲስ አበባ ሽንፈት
የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ሳይኖሩ ፤ በመጀመሪያ ደቂቃዎች ግብ አስተናግዶ ፤ በመጀመሪያ አጋማሽ ግብ ጠባቂውን በቀይ ካርድ ያጣው አዲስ አበባ ከተማ በተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ ላይ የእንቅስቃሴ ብልጫ ወስዶ በመጫወት 1-0 በሆነ ውጤት አሳዛኝ ተሸናፊ ሆኗል።
ዋና እና ምክትል አሰልጣኙን ጨምሮ አዲሱ የቡድኑ ቴክኒካል የዳይሬክተርን ሳይቀር በሙሉ በኮቪድ ምክንያት በጨዋታው ዕለት ማግኘት ያልቻለው አዲስ አበባ በምትካቸው የቡድኑ ሦስተኛ አምበል እና ግብ ጠባቂ ለሆነው ዳንኤል ተሾመ በሜዳ ላይ ለ90 ደቂቃዎች በአሰልጣኝነት የመምራት ኃላፊነትን በመስጠት ጨዋታውን ከውኗል።
በዚህ ብቻ ያላበቃው የአዲስ አበባ ፈተና ጨዋታው ከተጀመረ በኋላም ቀጥሏል። ገና በ13ኛው ደቂቃ ሳጥናቸው ውስጥ በሰሩት ጥፋት በተሰጠ የፍፁም ቅጣት ምት መመራት የጀመሩ ሲሆን ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ በ31ኛው ደቂቃ ደግሞ በተከላካያቸው ዘሪሁን አንሼቦ እና ግብ ጠባቂያቸው ዋኬኔ አዱኛ አለመናበብ በተፈጠረ አጋጣሚ ግብ ጠባቂያቸውን በቀይ ካርድ ለማጣት ተገደዋል።
ታድያ የእነዚህ ሁኔታዎች መደራረብ ለተመለከተ አዲስ አበባ ከተማዎች በቀሩት የጨዋታ ደቂቃዎች ሊቸገሩ ይችላል ብሎ ቢገመትም ሜዳ ላይ ያየነው እንቅስቃሴ ግን የተገላቢጦሽ ነበር።
አዲስ አበባ ከተማዎች በቁጥር ማነሳቸው ሳይበግራቸው ኳሱን በተሻለ መጠን በመቆጣጠር ተጋጣሚያቸውን ወደ ራሱ ሜዳ እንዲገፋ እና ያለ ኳስ ብዙ እንዲሮጥ በማድረግ ችለዋል። ይህን የበላይነት ወደ ግብ ዕድሎች በመቀየር ረገድ ግን ውስንነቶች ነበሩባቸው። በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች በድሬዳዋ ከተማም በኩል አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ መውጣቱን ተከትሎ ጨዋታውን በዕኩል የተጫዋች ቁጥር በሽንፈት ለመጨረስ ቢችሉም አመዛኙን ደቂቃ በጎዶሎ ሰው የተጫወቱት አዲስ አበባ ከተማዎች የተሻሉ እንደነበሩ መመስከር ይቻላል።
እርግጥ ሁኔታውን ከውጤት አንፃር ከመዘነው ጥሩ ባይባልም ከነበሩት ሁኔታዎች አኳያ ቡድኑ በዘጠና ደቂቃ ሜዳ ላይ ያሰየው ጥረት ግን ተስፋ የሚሰጥ ነበር ብሎ ማንሳት ይቻላል።
👉 ነገሮች መልክ እየያዙለት የመጡት ሀዲያ ሆሳዕና
በተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች የውድድር ዘመኑን የጀመረው እና የመጀመሪያ ድሉን ፍለጋ ሰባት የጨዋታ ሳምንት ድረስ ለመጠበቅ የተገደደው ሀዲያ ሆሳዕና አሁን ላይ እያንሰራራ ይገኛል።
በዘንድሮው አጀማመሩ ውጤቱ አይመር እንጂ ቡድኑ በእንቅስቃሴ ረገድ በአብዛኛዎቹ ጨዋታዎች የተሻለው ተጋጣሚ የነበረ ሲሆን መሰረታዊ ችግሩ የነበረው የግብ ዕድሎችን በጥራት መፍጠር እና የሚፈጠሩትን ጥቂት ዕድሎችን ወደ ግብ በመቀየር ረገድ የነበረበትን መጠነ ሰፊ ችግር ከደካማ አጀማመሩ ጀርባ የነበረው እውነታ ነበር።
በዚህ መንገድ የዘለቀው ጉዞ ግን በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች መሻሻሎችን አሳይቷል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ጠንካራውን ኢትዮጵያ ቡና የረታው ሆሳዕና በቀደሙት ሳምንታት ደግሞ ድሬዳዋ ከተማ እና መከለካያን ድል ማድረጉ አይዘነጋም።
ድል ባስመዘገበባቸው ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች እንደ መጀመሪያዎቹ ሳምንታት ሁሉ ተለዋዋጭነት ያለውን የጨዋታ መንገድ የተከተለው ሀዲያ ሆሳዕና አሁን ላይ በማጥቃቱ ረገድ እያሳየው በሚገኘው መሻሻል ሦስት ተከታታይ ድሎችን በማስመዝገብ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ቆይታውን በሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ ሆኖ አጠናቋል።
👉 አዳማ እና ማሸነፍ ታርቀዋል
በ2ኛ የጨዋታ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋርን ከረቱ ወዲህ የማሸነፍያው መንገድ ጠፍቷቸው የነበሩት አዳማ ከተማዎች ከአምስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ጠንካራውን ባህር ዳር ከተማን 1-0 በሆነ ውጤት በመርታት ከማሸነፍ ጋር የታረቁበትን ውጤት አስመዝግበዋል።
ብዙ የማያገባ እና ብዙ የማይገባበት የሆነው የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቡድን በሊጉ ከመሪዎቹ ፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ ሦስተኛው ጠንካራ የመከላከል ክፍል ባለቤት ሲሆን በማጥቃቱ ረገድ ደግሞ እንዲሁ ጅማ አባ ጅፋር እና መከላከያን በመብለጥ ሦስተኛ ደካማው የአጥቂ መስመር ባለቤት መሆኑ አጠቃላይ የቡድኑን አሁናዊ ሁኔታ በአግባቡ ይገልፃል።
ጠንካራ የመከላከል መስመር ባለቤት መሆን አንድ የሚያረጋግጥልን እውነታ ቢኖር ቡድኑ በቀላሉ ግቦች የማይቆጠሩበት መሆኑን ብቻ ሳይሆን እንደ አዳማ ከተማ ላለ ገና የአጥቂ መስመሩ ዕድሎችን ወደ ግብነት የመቀየር ንፃሬው ደካማ ለሆነ ቡድን አንድ ግብ በጨዋታ ማስቆጠር በራሱ ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዞ መውጣት እንደሚያስችለው የሚያሳይም ጭምር ነው። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ባህር ዳር ከተማን የረቱበት ጨዋታ ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ነው።
በ12 ነጥቦች ደረጃውን ወደ 8ኛ ማሻሻል የቻለው የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኙ አዳማ በቀጣይ በማጥቃቱ ረገድ ያሉበትን ውስነቶች በአፋጣኝ የሚያሻሽል ከሆነ ከያዘው ስብስብ አንፃር በሰንጠረዡ አናት ከመፎካከር ሊያግደው የሚችል አንዳችም ነገር እንደማይኖር ቁጥሮች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።
👉 ከደጋፊዎቹ የታረቀው ሀዋሳ ከተማ
በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ እየተመሩ አዲሱን የውድድር ዘመኑን የጀመሩት ሀዋሳ ከተማዎች ሊጉን በድል ቢጀምሩም በሂደት ግን ወጥ የሆነ አቋምን ለማሳየት ተቸግረው ቢታዩም በመጨረሻዎቹ ጥቂት ሳምንታት የተሻለ መነቃቃትን በማሳየት ላይ ይገኛሉ።
በእነዚህ የ9ኛ ሳምንታት የሊጉ ቆይታ ውስጥ ከሀዋሳ ጋር የሚነሳው ዋነኛ ጉዳይ የነበረው በክለቡ ደጋፊዎች እና በክለቡ አባላት መካከል ተፈጥሮ የነበረው ልዩነት ነበር። በተለይ ከሮድዋ ደርቢ ድል ማግስት በነበሩት ጨዋታዎች የክለቡ ደጋፊዎች በክለባቸው ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን ሲያሰሙ የቆዩ ሲሆን በአንድ አጋጣሚም ይህ ተቃውሞ ከመጠን አልፎ በደጋፊዎች እና በተጫዋቾች መካከል ቡጢ እስከመማዘዝ ድረስ ደርሶ ነበር።
ታድያ የእነዚህ ሁሉ ተቃውሞዎች መነሻ የነበረው ቡድኑ ውጤት ባጣባቸው ጨዋታዎች መጠኑ ቢለያይም የክለቡ ደጋፊዎች እየተከተለ በሚገኘው የጨዋታ መንገድ ደስተኛ ካለመሆናቸው የመነጨ እንደሆነ ሲገልፁ ይደመጣል። ይህን ሂደትም ለመቀልበስ የተወሰኑ ደጋፊዎች ወደ ክለቡ የልምምድ ሜዳ አምርተው ከቡድኑ አባላት ጋር ውይይት ካደረጉ ወዲህ በዚህ ሂደት ላይ መሻሻሎችን እየተመለከትን እንገኛለን።
በተለይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በተሸነፉበት ጨዋታ ጀምሮ በነበሩት ጨዋታዎች ደጋፊው ይበልጡኑ ከክለቡ ጎን ሆኖ ቡድኑን ለተሻለ ውጤት ሲያበረታታ እየተመለከትን እንገኛል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አርባምንጭ ከተማን ሲረቱ በቁጥር ከወትሮው በጣም በርከት ያሉ የክለቡ ደጋፊዎች በክለቡ ቀለማት ደምቀው ቡድናቸውን ለ90 ደቂቃ ሲያበረታቱ ተመልክተናል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የሀዋሳ ከተማ ቡድን አባላት በሜዳው የተገኙትን የክለቡን ደጋፊዎችን ሲያመሰግኑ መታየታቸው ሻክሮ የነበረው ግንኙነት ስለመሻሻሉ ዓይነተኛ ማሳያ ነበር።
በቡድኑ አባላት እና በደጋፊዎች መካከል አሁን ላይ የሰፈነው ጤናማ ግንኙነት ሀዋሳ በቀጣይ በሚያደርገው ጉዞ ይበልጥ ሊያግዘው እንደሚችል ሲጠበቅ የተሻለ ድጋፍ ሊያገኙ የሚችሉበት የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የውድድር ቆይታ በዚህ ወቅት መጠናቀቁ ለሀዋሳ ከተማዎች የሚያስቆጭ አጋጣሚ ሆኗል ማለትም ይቻላል።