​የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሽኝት መርሐ-ግብር ተከናውኗል

ምሽቱን በተደረገው የዋሊያዎቹ የሽኝት መርሐ-ግብር ላይ የተገባውን ቃል እና የነበሩ ሁነቶችን እንዲህ እናስነብባችኋለን።

ዛሬ ምሽት በስካይላይት ሆቴል ከስምንት ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ወደ ካሜሩን ለሚያቀናው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት የተደረገው የሽኝት ፕሮግራም የተለያዩ የመንግሥት ባለስልጣናት ፣ የእግር ኳሱ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶች በተገኙበት የተከናወነ ነበር። የቡድኑ አባላት ወደ ሆቴሉ መድረሳቸውን ተከትሎ በይፋ በጀመረው ሥነ-ስርዓት በርካታ መልዕክቶች የተላለፉ ሲሆን ንግግር በማድረግ ቅድሚያውን የወሰዱት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዳሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ነበሩ።

“ብሔራዊ ቡድኑ ይህንን ታሪክ ሲሰራ ነገሮች አልጋ በአልጋ አልነበሩም” ያሉት ፕሬዘዳንቱ አመራሩ እና ሥራ አስፈፃሚው ከባባድ ውሳኔዎችን በማሳለፍ በጋራ ቆሞ ውጤቱ እንዲገኝ ስላበረከተው አስተዋፅዖ አንስተው በሂደቱ ላይ ተሳትፎ ለነበራቸው አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። በማብራሪያቸው ውስጥ ካነሷቸው ዋና ሀሳቦች ውስጥም ብሔራዊ ቡድኑን ለዝግጅት ወደ ሳውዲ አረቢያ እንዲያመራ ለማድረግ ከጫፍ ቢደሩስም የኮቪድ ወረርሺኝ በማገርሸቱ ሳቢያ ሳይሳካ መቅረቱን ተናግረዋል። 500 ደጋፊዎችን ይዞ ለመሄድ እየተሰራ ሰለመሆኑ ጠቁመውም ከተሳትፎ ባለፈ የስፖርት መርሆችን በጠበቀ መልኩ የውድድሩ መድረክ ላይ የሀገራችንን አንድነት ለማሳየት እና የስፖርት ዲፕሎማሲ ሥራ ለመስራት መታሰቡንም አያይዘው ገልፀዋል።

በመቀጠል ውድድሩ ሲቃረብ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ለህዝቡ እንደሚቀርብ የተገለፀ እና ብሔራዊ ቡድኑ በማጣሪው ስላደረገው ጉዞ የሚተርክ የ45 ደቂቃ ዘጋቢ ፊልም ለታዳሚው ቀርቧል።

ከታዳሚዎች መካከል በዕንግድነት የተገኘው አርቲስት ታማኝ በየነ ከዘጋቢ ፊልሙ መጠናቀቅ በኋላ ተሰብሳቢውን ያነቃቃ እና ለብሔራዊ ቡድኑ ተመራጮች የሞራል ስንቅ የሚሆን ቀስቃሽ ንግግር አድርጓል። በመቀጠል የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በአጋርነት አብረውት ለሚሰሩ ድርጅቶች ስጦታ ያበረከተ ሲሆን መንግሥት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ላደረገው ድጋፍ የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ወታደራዊ ሰላምታ ሲሰጡ የሚያሳይን ምስል ከኢፊዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ምስል ጋር በማድረግ ለስፖርት እና ባህል ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ቀጀላ መርዳሳ አስረክቧል።

ቀጣዩ መርሐ-ግብር የነበረው የሰንደቅ ዓላማ ርክክብ ነበር። በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ፣ አምበሉ ጌታነህ ከበደ እና የቡድን መሪው አቶ አበበ ገላጋይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ  ከስፖርት እና ባህል ሚኒስትር ክቡር ቀጀላ መርዳሳ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እጅ ተረክበዋል።

በመቀጠል ክቡር አምባሳደር መስፍን ቸርነት የኢፊዲሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዲኤታ ፣ የስፖርት እና ባህል ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ቀጀላ መርዳሳ በተከታታይ የብሔራዊ በድኑን የካሜሩን ጉዞ አስመልክተው ቡድኑ ሊኖረው ስለሚገባው ሀገራዊ ስሜት ጋር የተያያዘ ንግግር አድርገዋል። የኢፊዲሪ ፕሬዚዳንት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴም በመርሐ-ግብሩ ላይ ባይገኙም በተንቀሳቃሽ ምስል በተላለፈ መልዕክታቸው ዋሊያዎቹን የሚያበራተቱ ሀሳቦችን አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም የዕለቱ መርሐ ግብር መዝጊያ የሆነው የኬክ መቁረስ ሥነስርዓት መከናወን ሲጀምር በድጋሚ ወደ መድረክ የመጡት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ዋሊያዎቹ በውድድሩ ከምድባቸው ማለፍ ከቻሉ ፌዴሬሽኑ የዘጠኝ ሚሊዮን ብር ሽልማት እንዳዘጋጀ አብስረዋል። ከዚህ ውጪ የፌዴሬሽኑ አጋር የሆነው ቡና ኢንተርናሽናል ባንክም ለዋሊያዎቹ የሁለት ሚሊዮን ብር ጉርሻ ማድረጉ በመድረኩ ተገልጿል።

በ33ኛው የካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ ነገ ወደ ያውንዴ በመብረር እስከ ውድድሩ ጅማሮ ዝግጅቱን እያደረገ እንደሚቆይ ይጠበቃል።