የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአንደኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ሁለት ጨዋታዎች ረፋድ ተደርገው አዲስ አበባ ከተማ ባህርዳር ከተማን 1-0 ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን 2-1 አሸንፈዋል፡፡
ገና ከጅምሩ ተመጣጣኝ ፉክክርን ማሳየት የጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ እና ባህርዳር ከተማ ጨዋታ በአመዛኙ የጨዋታዎቹ ደቂቃዎች በመሀል ሜዳ ላይ ያጋደሉ ነበሩ፡፡ ኳስን መሠረት ባደረገ መልኩ መንገድ ቡድኖቹ የተንቀሳቀሱ ቢሆንም ወደ ጎል የሚደርሱበት ሂደት ግን ደካማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በአንድ ሁለት ቅብብል ከአማካይ ክፍል ዕድሎችን በመፍጠር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የማይቸገሩት አዲስ አበባ ከተማዎች የነበሩ ቢሆንም ከፊት የተሰለፉት አጥቂዎች ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ በቀላሉ እንዲያመክኑ አድርጓቸዋል፡፡
በተለይ ብሩክታዊት ግርማ እና አሪያት ዲቦ አግኝተው ያመከኗቸው ግልፅ ዕድሎች ማሳያዎች ናቸው፡፡ አርያት ኦዶንግ በረጅሙ ከቀኝ የሜዳው ክፍል ያገኘችውን ኳስ ወደ ጎልነት ለወጠችሁ ተብሎ ሲጠበቅ የባህር ዳር ከተማዋ ግብ ጠባቂ ሽብሬ ኮንካ በግሩም ሁኔታ የያዘችባት አጋጣሚ ከሁሉም የላቀው ሙከራ ነበረ፡፡በአንፃሩ አዲስ አዳጊው ባህርዳር ከተማ በዛሬው ጨዋታ አሰልጣኝ ሠርካዲስ እውነቱን በግል ጉዳይ ቡድኑን መምራት ባትችልም ሜዳ ላይ ያሳዩትን የነበረው ጥረት ግን የሚደነቅ ነበረ፡፡ ረጃጅም ኳስን መሠረት ባደረገ እና ከፊት ለተሰለፉት ለምስር ኢብራሂም እና ሜላት ደመቀ ኳሶችን በማድረስ ጥቃትን ለመሰንዘር ጥረዋል፡፡ ምስር ከሳጥን ውጪ መትታ ስርጉት የያዘችበት እና ሜላት ደመቀ በተመሳሳይ አግኝታ በቀላሉ ማምከን የቻለቻት ተጠቃሿ ሙከራ ነበረች፡፡ሁለቱም ቡድኖች ጎል ጋር ለመድረስ አለመቸገራቸውን ማስተዋል ብንችልም ከአጨራረስ አንፃር ፍፁም ደካሞች በመሆናቸው አጋማሹ ያለ ጎል ተገባዷል፡፡
ከዕረፍት መልስ ጠንካራ የሜዳ ላይ ተፎካካሪ መሆናቸውን ማሳየት የጀመሩት የአሰልጣኝ የሺሐረግ ለገሰ አዲስ አበባ ከተማዎች 55ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አግኝተዋል ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ዘንድሮ ቡድኑን መቀላቀል የቻለችው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቿ አሪያት ኦዶንግ በአንድ ሁለት ቅብብል የደረሳትን ኳስ በድንቅ አጨራረስ ወደ ጎልነት ለውጣው ቡድኗን መሪ አድርጋለች፡፡
ባህርዳር ከተማዎች ምንም እንኳን በተደጋጋሚ በተለይ ከሜላት ደመቀ እግር ከሚነሱ የጠሩ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለማግኘት ቢታትሩም በተለይ ትዕግስት ወርቁ እግር ስር የሚገቡ ኳሶች ይባክኑ ስለነበረ ግብ በቀላሉ ለማግኘት አልቻሉም፡፡ በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማዎች በዕለቱ ጥሩ በነበረችው ብሩክታዊት አየለ እና እምወድሽ አሸብር አማካኝነት ተጨማሪ ዕድሎችን ቢያገኙም ተጨማሪ ግብ ሳንመለከትበት ጨዋታው 1-0 በመዲናይቱ ክለብ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የቤቲካ የጨዋታ ሽላማትን ለአጥቂዋ ብሩክታዊት አየለ አበርክቷል፡፡
5፡10 ሲል በጀመረው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ገና የጨዋታው ደቂቃዎች ሳይጋመሱ ነበር በጊዜ ግቦችን መመልከት የቻልነው። ሀዋሳ ከተማን ለቃ ኤሌክትሪክን የተቀላቀለችው አጥቂዋ ዓይናለም አሳምነው ከቀኝ በኩል በቀጥታ ወደ ጎል የመታችሁ ኳስ በ2ኛው ደቂቃ ከመረብ አርፎ የአሰልጣኝ መሰረት ማኔ ቡድን ቀዳሚ መሆን ችሏል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስን የመከላከል አደረጃጀት በደንብ የተረዱ የመሰሉት ቀያይ ለባሾቹ በ4ኛው ደቂቃ ዕድላዊት ተመስገን አክርራ ከሳጥኑ ጠርዝ መትታ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ወደ 2-0 መሪነት አሸጋግራለች፡፡
ኳስን መስርቶ በመጫወት እና በቅብብል በተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫ ከመውሰድ የፈረሰኞቹ እንስቶች የበላይ ቢሆኑም ደካማ የነበረው የአጨራረስ እንዲሁም ደግሞ የአቋቋም ስህተት ይታይባቸው ስለነበረ በቀላሉ ጉልበት አዘል ለነበሩት ተጋጣሚያቸው እጅ ለመስጠት ተገደዋል፡፡ ይሁን እንጂ በመጀመሪያ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ሁለት ጎሎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-0 እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
ሴት ተጫዋቾች እንደመሆናቸው እና ፀሀዩዋ እጅጉን ክርር ብላ ለመጫወት አዳጋች ሆና በታየችበት የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በንፅፅር ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳ ላይ የነቃ ተሳትፎን በማድረግ እና በተደጋጋሚ በተጋጣሚያቸው ላይ ፈታኝ የነበረን የሜዳ ላይ ብቃት ማንፀባረቅ የቻሉበት ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ከፊት ተሰልፈው መልካም እንቅስቃሴን ሲያደርጉ የነበሩት አጥቂዎቹ ዳግማዊት ሰለሞን እና ጋብርላ አበበ በዚህኛው አጋማሽ በመከላከሉ ደካማ ለነበሩት የኤሌክትሪክ የተከላካይ ክፍል ራስ ምታት ሲሆኑባቸው ተስተውሏል፡፡ለዚህም ማሳያ 82ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ አቅጣጫ በረጅሙ የተሻማን ቅጣት ምት ግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለ በአግባቡ መቆጣጠር ባለመቻሏ ጋብሬላ አበበ አግኝታው ወደ ጎልነት ለውጣው ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ ጨዋታ መልሳለች፡፡
ጎሉን ካስቆጠሩ በኋላ በይበልጥ ጫና ለማሳደር ቢችሉም ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ግን ተቸግረው ታይቷል፡፡ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ምንትዋብ ዮሐንስ እና አይዳ ዑስማን ያገኙትን አጋጣሚ አስቆጠሩ ሲባል በተለይ የምንትዋብ ኳስ የግቡ ቋሚ መልሶባት በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃ የተቆጠሩ ጎሎች ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-1 አሸናፊ በማድረግ ተጠናቋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ልሳን የሴቶች ስፖርት የቤቲካ የጨዋታ ሽልማትን ለኝቦኝ የን ሰጥቷል፡፡