ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ከጫፍ ደርሷል

በፕሪምየር ሊጉ ደካማ የውድድር ተሳትፎ ላይ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በነፃ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ለመቀላቀል ተቃርቧል።

\"\"

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከታችኛው የሊግ ዕርከን በማደግ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ተመልሶ በሊጉ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ እየተመራ በሁለተኛው ዙር በርካታ ዝውውሮችን ፈፅሟል። አሁን ደግሞ ከክለቡ ጋር ልምምድ እየሰሩ የሚገኙ ሁለት የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ከጫፍ ስለ መድረሱ ሶከር ኢትዮጵያ ለማወቅ ችላለች።

ፍፁም ገብረማርያም ቀዳሚው ተጫዋች ነው። ከዩኒቨርስቲ ውድድሮች ከተገኘ በኋላ ለሙገር ሲሚንቶ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ መቻል እና ሰበታ ተጫውቶ ያሳለፈው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹ የቀድሞው ክለቡን ለመቀላቀል በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ንግግር እያደረገ ይገኛል።

ሴኔጋላዊው አጥቂ ፓውል አሎን ጎሜዝም ክለቡን የሚቀላቀለው ሌላኛው ተጫዋች ሆኗል። 30ኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው እና በሞሪታኒያዎቹ ኤኤሲ ኬንዲያ እና ኤኤሲ ካሳራ በተባሉ ክለቦች ብቻ ስለመጫወቱ መረጃዎችን ያገኘነው ተጫዋቹ ባደረገው የሙከራ ጊዜ አመርቂ ሆኖ በመገኘቱ ክለቡን ሊቀላቀል ከጫፍ ደርሷል።

በትላንትናው ዕለት በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት የገጠመው ቡድኑ በሊጉ በስምንት ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

\"\"