ለገጣፎ ለገዳዲዎች በአዲሱ ፈራሚያቸው ሱለይማን ትራኦሬ ድንቅ ግቦች ድሬዳዋ ከተማን 2-1 በመርታት በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ድላቸውን አጣጥመዋል።
በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ ያን ያህል የሚታይ ብልጫ ባይታይበትም የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በማድረጉ በኩል የተሻሉ የነበሩት ለገጣፎዎች በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ሁለት አደገኛ የግብ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። በቅድሚያ 8ኛው ደቂቃ ላይ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ በግንባሩ ገጭቶ በትክክል ያላራቀውን ኳስ ያገኘው በለገዳዲ መለያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው አጥቂው ሱለይማን ትራኦሬ ያገኘውን ኳስ ከልሎ መሬት ለመሬት በመምታት ያደረገውን ግሩም ሙከራ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን መልሶበታል። ያንኑ ኳስ ሲመለስ ያገኘው ተስፋዬ ነጋሽም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ኳሱን እንዳይጠቀምበትም የተከላካዩ ኢያሱ ለገሠ ሚና ከፍተኛ ነበር። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነትም ተስፋዬ ነጋሽ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሱለይማን ትራኦሬ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ የግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተጨምሮበት የግቡን የቀኝ ቋሚ ገጭቶ ወጥቶበታል።
ቀስ በቀስ የማጥቃቱን እንቅስቃሴ የተቀላቀሉት ድሬዎች ፈታኝ ሙከራ ለማድረግ ይቸገሩ እንጂ በተለይም በቀኙ የሜዳ ክፍል ከእንየው ካሳሁን እና ኤልያስ አህመድ በሚነሱ ኳሶች በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። 27ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ አህመድ ወደ ቀኙ የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ ከሳጥን አጠገብ አሻምቶት አጥቂው ቻርለስ ሙሴጌ በግንባሯ ሊገጭ ሲሞክር በጊዜ አጠባበቅ ስህተት ያመለጠው ኳስ የተሻለው የግብ ዕድላቸው ነበር።
በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ እየተወሰደባቸው የመጡት ለገጣፎዎች 36ኛው ደቂቃ ላይ ባልታሰበ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ግብ ሊያስቆጥሩ ተቃርበው ነበር። ከራሳቸው የሜዳ ክፍል የተሻገረውን ኳስ የድሬው ተከላካይ አሳንቴ ጎድፍሬድ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ ኳሱን ያገኘው በአጋማሹ ልዩነት ፈጣሪ በመሆን ደምቆ የታየው ሱለይማን ትራኦሬ በግራ እግሩ ከግብ ጠባቂው ከፍ አድርጎ የሞከረው ኳስ የግቡን የላይ አግዳሚ ገጭቶ ወጥቶበታል።
ከዕረፍት መልስ ካለፉት ጨዋታዎች እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት ለገጣፎዎች ጨዋታውን መቆጣጠር ሲችሉ 55ኛው ደቂቃ ላይ በርካታ ሙከራዎችን ሲያደርግ የነበረው አጥቂያቸው ሱለይማን ትራኦሬ ከራሱ የግብ ክልል በረጅም የተሻማለትን ኳስ በመቆጣጠር እና እጅግ ድንቅ በሆነ ክህሎት ተከላካዮችን አሸማቆ በማለፍ ግብ አስቆጥሮ ለገጣፎን መሪ ሲያደርግ በሦስት ደቂቃዎች ልዩነትም ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ የዕለቱ ኮከብ ተጫዋች የነበረው ሱለይማን ትራኦሬ ከግራው የሳጥኑ ክፍል ላይ ተጫዋች አታልሎ በማለፍ መሬት ለመሬት አክርሮ በመምታት መረቡ ላይ አሳርፎት የክለቡን መሪነት አጠናክሯል።
በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ የተቀዛቀዙት ብርቱካናማዎቹ 69ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም ጌታቸው ተቀይሮ በገባበት ቅፅበት በጥሩ ሩጫ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ባመከነው ኳስ የተሻለውን የግብ ዕድል ሲፈጥሩ በሴኮንዶች ልዩነት ግን ተጨማሪ ግብ ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር። የለገዳዲው አማኑኤል አረቦ ከረጅም ርቀት መሬት መሬት አክርሮ በመምታት ያደረገው ግሩም ሙከራ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ወጥቶበታል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ድሬዳዋ ከተማዎች የለገጣፎን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት አልፈው ለመግባት ሲቸገሩ 93ኛው ደቂቃ ላይ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ በድንቅ ዕይታ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ቢንያም ጌታቸው በግሩም ቅልጥፍና በአየር ላይ እንዳለ አስቆጥሮት ድሬዎችን ለባዶ ከመሸነፍ ሲያድን በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ የለገጣፎው ግብጠባቂ ኮፊ ሜንሳህ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተወግዶ ቀሪዎቹን ሴኮንዶች ተቀይሮ የገባው አጥቂው ካርሎስ ዳምጠው በግብ ጠባቂነት ሲያሳልፍ ለገጣፎዎችም ጨዋታውን በማረጋጋት ውጤቱን አስጠብቀው 2-1 በመርታት ከ 15 ጨዋታዎች በኋላ በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ድላቸውን አሳክተዋል።