ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንግድ ባንክ በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎች አርባምንጭን ረቷል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት የመጨረሻ ስድስተኛ ጨዋታ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ በንግድ ባንክ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን የመጀመሪያው ዙር የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ላይ መደረግ ከጀመረ ሁለተኛ ቀኑ ላይ የሚገኝ ሲሆን 10፡00 ሰአት ሲል አርባምንጭ ከተማን ከአርባምንጭ ከተማ የመጨረሻ የሳምንቱ ጨዋታ ተደርጓል፡፡በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የጨዋታ የሀይል ሚዛናቸውን ወደ አርባምንጭ የግብ ክልል በማስጠጋት ለመጫወት የሞከሩት ንግድ ባንኮች ቢሆንም በተለይ በመጀመሪያው አስር ደቂቃዎች አርባምንጮች በጥብቅ የመከላከል መንገድ ያደረጉት ሁነኛ አጨዋወት በቀላሉ እጅ እንዳይሰጡ አድርጓቸዋል፡፡

ሎዛ አበራ ፣ መዲና ዐወል እና ዮርዳኖስ ምዑዝን ከፊት በማሰለፍ ቀዳዳ ፍለጋ ጥረት ለማድረግ የሞከሩት ንግድ ባንኮች በአንድ ሁለት ቅብብል ጎል ለማስቆጠር ከጣሩበት ሂደት ይልቅ ከርቀት ግን ግብ አግኝተዋል፡፡16ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የአርባምንጭ የግብ አካባቢ የቀኝ ተከላካዩዋ አለምነሽ ገረመው አክርራ ወደ ጎል ስትመታው የቀድሞው ክለቧን የገጠመችው ግብ ጠባቂዋ ምህረት ተሰማ ለመመለስ ጥረት ስታደርስ የግቡ ቋሚ ብረት ጀርባዋን ገጭቶ ከመረብ በማረፉ ንግድ ባንክ መሪ መሆን ችሏል፡፡

በአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ የሚመራው አርባምንጭ ከተማ ኳስን በግሩም የቅብብል ሂደት ግብ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም ወደ ግብ ክልል ሲደርሱ ያደርጉት የነበረው የሙከራ ሂደት የተቀዛቀዘ መሆኑ በቀላሉ እንዲያመክኑ አድርጓቸዋል፡፡በተለይ አጥቂዎቹ ወርቅነሽ ሜልሜላ እና ድንቅነሽ በቀለ የሚያገኙትን መልካም አጋጣሚዎችን አለመጠቀማቸው እና ፍፁም መረጋጋት ተስኗቸው መታየቱ ሁለተኛ ግብ በተቃራኒው እንዲቆጠርባቸው ሆኗል፡፡ከመከላከያ ንግድ ባንክን በክረምቱ ከተቀላቀለች በኋላ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የምስራቅ አፍሪካ የውድድር መድረክ ደምቃ የነበረችሁ መዲና ዐወል ከሳጥን ውጪ የተከላካዮች እና የምህረት ተሰማን ስህተት በደንብ በማስተዋል ግብ አስቆጥራ ቡድኑን ወደ 2ለ0 ማሸጋገር ችላለች፡፡

ከእረፍት መልስ በቀጠለው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በዚህኛው አጋማሽ ተመጣጣኝ የሚመስል አጨዋወትን መመልከት ችለናል፡፡በሰናይት ቦጋለ ከሚመራው የመሀል ክፍሉ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር በመስመር ያጋደለ እንቅስቃሴን ለማድረግ ሲታትሩ የታዩት ንግድ ባንኮች በተለይ ወደ ግራ መስመር የእፀገነት ብዙነህን ቦታ ተመራጭ አድርገው ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም ለወትሮ ንቃት የጎደላቸው የሚመስሉት የፊት ተሰላፊዎች ሊጠቀሟቸው አልቻሉም፡፡

በአንፃሩ ብርቱ ተፎካካሪ በመሆን እጅግ አስደናቂ አቋማቸውን ሜዳ ላይ ሲያስመለክቱን የታዩት አርባምንጭ ከተማዎች በረጃጅም እና በቅብብሎሽ ወደ ባንክ የሜዳ ክፍል መድረስ ቢችሉም የመጨረሻ የውሳኔ አሰጣጣቸው ቀዝቀዝ ያለ መሆኑ ግብ ላለማግኘታቸው ማሳያ ነበረ፡፡በዚህም ወርቅነሽ ከርቀት መታ ለጥቂት የወጣባት ምናልባት ጠንከር ያለው የክለቡ ሙከራ ነበረች፡፡ በሌላ በኩል የምስራች አሻምታ አለምነሽ በግንባር ገጭታ ለጥቂት የወጣባት እና ሎዛ አበራ ከርቀት ሞክራ በግቡ አግዳሚ የወጣበት የቡድኑ ጠንካራው አጋጣሚ ነበር ማለት ይቻላል ጨዋታው ሉጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት መዲና ዐወል አንድ ለአንድ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ ያልተጠቀመችበት አስቆጪው አጋጣሚ ነበረ፡፡ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳንመለከትበት በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ልጆች 2ለ0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

 

የንግድ ባንኳ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ሰናይት ቦጋለ በልሳን የሴቶች ስፖርት የቤቲካ የጨዋታ ኮከብ ሽልማትን አግኝታለች፡፡