በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ በታዩ የዲሲፕሊን ጥሰቶች ላይ ውሳኔ ሲሰጥ ሀዋሳ ከተማ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበታል፡፡
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተደርገው ከትናንት በስቲያ ዓርብ መጠናቀቃቸው ይታወሳል፡፡ ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ በሚል ለረጅም ጊዜ በእረፍት የሚዘልቀው ፕሪምየር ሊጉ በዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ በታዩ የዲሲፕሊን ጥሰቶች ላይ የሼር ካምፓኒው የውድድር እና ስነ ስርአት ኮሚቴ አሳልፏል፡፡ ሀዋሳ ከተማ በያዝነው ሳምንት የመጨረሻ የሳምንቱ መዝጊያ ጨዋታውን አድርጎ አርባምንጭ ከተማን 1ለ0 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የክለቡ ደጋፊዎች እና የደጋፊ አስተባባሪዎች ከፖሊስ ጋር ግጭት ስለመፍጠራቸው እና ድንጋይ ስለመወርወራቸው እንዲሁም የተለያዩ የስታዲየሙ ንብረቶች ላይ ጉዳት ስለማድረሳቸው ሪፖርት በመቅረቡ ክለቡ የ75 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተላልፎበታል፡፡ ክለቡ በሚቀርብበት የዋጋ ተመን መነሻነት ንብረቱ ተሰልቶ ክፍያ እንዲፈፅምም በቅጣቱ ተካቷል፡፡
በተጫዋች ቅጣት ዜና ደግሞ ድሬዳዋ ከተማ ከ አዲስ አበባ ከተማ ሲጫወት በሁለት ቢጫ ከሜዳ የተወገደው አብዱለጢፍ መሀመድ እና በዚህው ጨዋታ ቀይ ካርድ ተመልክቶ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማው ግብ ጠባቂ ዋኬኔ አዱኛ የአንድ ጨዋታ ቅጣት ሲጣልባቸው ዋኬኔ ተጨማሪ የ3 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበታል፡፡ ሀዋሳ ከተማ አርባምንጭን 1ለ0 ሲያሸንፍ ግብ ካስቆጠረ በኋላ በውስጥ ልብሱ ሀይማኖታዊ ምስል አሳይቶ የነበረው ብሩክ በየነ የ3 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ሲተላለፍበት የባህርዳር ከተማው ግርማ ዲሳሳ ክለቡ በአዳማ በተረታበት ጨዋታ ቀይ በማየቱ የሦስት ጨዋታ የ3 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበታል፡፡ ሀዋሳ ከተማ እና ባህርዳር ከተማ ደግሞ እንደ ቡድን ባዩት የቢጫ ካርድ ብፋት የ5 ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡