የመጨረሻው የፅሁፋችን ክፍል ሌሎች ትኩረት የሳቡ ሁነቶች ተካተውበታል።
👉 የሀዋሳ ከተማ የሊጉ ቆይታ መጠናቀቅ
ባለፉት ዘጠኝ የጨዋታ ሳምንታት ሰባ ሁለት ጨዋታዎችን ማስተናገድ የቻለችው ሀዋሳ ከተማ ቆይታዋን አጠናቃ በቀጣይ ሊጉ ከአፍሪካ ዋንጫ ሲመለስ የማስተናገድ ተራውን ለአዳማ ከተማ የምታስረክብ ይሆናል።
የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም የሊጉ የመጀመሪያ ዘጠኝ ሳምንታት ቆይታ ሲታወስ ቀዳሚ ጉዳይ ሆኖ የሚወሳው የመጫወቻ ሜዳው ጉዳይ መሆኑ አያጠያይቅ። ብዙ የተባለበት የመጫወቻ ሜዳው ለጨዋታ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደነበር ለመታዘብ ችለናል።
ከዚህ ውጪ ባሉ መመዘኛዎች ግን በጥቅሉ የሀዋሳ የሊጉ ቆይታ ጥሩ በሚባል መልኩ የሚወሳ ይሆናል ። መልካም የሚባል ትውስታዎች የሰጠን የሀዋሳ ከተማ የሊጉ ቆይታ ከነታሪኮቹ ለቀጣዩ ባለተራ ዕድሉን የሚያስረክብ ይሆናል።
👉 የደጋፊዎች ባነር ፋሽን
ሊጋችን የቴሌቪዢን ስርጭት ሽፋን ማግኘቱን ተከትሎ ጎልቶ የመታየት ዕድል ካገኙ አካላት መካከል ደጋፊዎች ይጠቀሳሉ። የአለባበስ ፣ የአጨፋፈር እና ሌሎች የድጋፍ መንገዶቻቸው ደግሞ በየጨዋታው ላይ እንደሚኖረው ንባራዊ ሁኔታ ይበልጥ ትከረትን እንዲስቡ ሲያደርጋቸው ይታያል። በዚህ የውድድር ዘመን ደጋፊዎች ከአምናው በላቀ ቁጥር ወደ ስታዲየም መግባት መጀመራቸውን ተከትሎ በተግባራቸው የመነጋገሪያ ርዕሶችን ሲፈጥሩ ይታያል። በተለይም ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት የወልቂጤ ደጋፊ የሆነች እንስት የጌታነህ ከበደን መለያ ለማግኘት ለተጫዋቹ የጠየቀችበት ፅሀፍ ያሰበችውን ያሳካላት መሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ ትከረትን ስቦ ነበር።
ይህንን ተከትሎ በተከናወነው የዘጠነኛ ሳምንት አብዛኞቹ ጨዋታዎች ላይ የደጋፊዎች የመለያ እና ሌሎች ጥያቄዎች የሚንፀባረቅባቸው ፅሀፎች በተደጋጋሚ ሲታዩ ተስተውሏል። ከእነዚህ መሀል ለፋሲል ከነማዎቹ ተጫዋች በረከት ደስታ እና ለአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የቀረበው የኬክ መቁረስ ጥያቄ ብቻ ምላሽ አግኝቷል። በጥቅሉ ሲታይ መሰል ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ውጪ ያሉ ሁነቶች እንደፋሽን ብቅ ማለታቸው ለውድድሩ ድምቀት መሆናቸው ባይካድም የሁኔታው መደጋገም እና ተመሳሳይ ሆኖ መታየቱ ነገሩን ግዴታ የሆነ ያህል ከማስመሰሉም በላይ አሰልቺ እንዲሆን በር የከፈተ ሆኖ አልፏል።
👉 የስታዲየሙ ፖውዛ እና 13 ደቂቃ
በ 8ኛው ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር ከሰበታ ከተማ እንዲሁም በ 9ኛው ሳምንት በተመሳሳይ ጅማ አባ ጅፋር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች በወቅቱ በነበረው ከፍተኛ ነፋስ መነሻነት የስታዲየም መብራት በመጥፋቱ ጨዋታዎቹ መቋረጣቸው ይታወሳል።
በሁለቱም አጋጣሚዎች የተቋረጡት ጨዋታዎች ከ13 ደቂቃዎች መቋረጥ በኋላ የመቀጠላቸው ነገር አስገራሚ ግጥምጥሞሽ ሲሆን በአስገራሚ መልኩ ሁለቱም መብራት በጠፋባቸው ጨዋታዎች ጅማ አባ ጅፋር የነበረባቸው ጨዋታዎች መሆናቸው አስገራሚ ያደርጋቸዋል።
ከዚህ አጋጣሚ ውጪ ፓውዛዎቹ ወደ ሥራ እንዲመለሱ የተደረገው ርብርብ በድጋሚ ምስጋና የሚቸረው ሆኖ አግኝተዋል። ችግሩ በ13 ደቂቃዎች ባይፈታ እና ከ15 ደቂቃ የዘለለ ጊዜን ቢወስድ የሱፐር ስፖርት ቀጥታ የስርጭት ሽፋን ሊቋረጥ የሚችልበት ዕድል የነበረ መሆኑ ደግሞ ችግሩን ለመፍታት የተደረገው ጥረት ረጅም ጊዜ ያለማስጠበቁ ዋጋ ከፍ ያለ መሆኑን ያስረዳናል።
👉 እነ ልጥፍጥፍ ተመልሰዋል
በሊጉ በተለይ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከሀገር በቀሉ “ጎፈሬ” የትጥቅ አቅራቢ ድርጅት ጋር ክለቦች ይፋዊ ስምምነቶችን እየፈፀሙ መገኘታቸውን ተከትሎ በመለያ ዙርያ የሚነሱ አሉታዊ ነገሮች እየቀነሱ መጥተዋል።
አምና በተለይ የሊጉን ገፅታ በጉልህ ያጎድፉ ከነበሩ ነገሮች መካከል ዋነኛው የነበረው በአንዳንድ ተጫዋቾች መለያ በስተጀርባ እንመለከታቸው የነበሩ በፕላስተር የተለጣጠፉ መለያዎች ጉዳይ ነበር። ዘንድሮ በመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንታት አካባቢ በወልቂጤ ከተማ መለያ ላይ ከተመለከትነው መሰል ሂደት ውጪ በስፋት ከዚህ አሰራር ተላቀን ብንቆይም በ9ኛ ሳምንት ይህን ነገር ዳግም ተመልክተናል።
ጅማ አባ ጅፋር ከቅዱስ ጊዮርጊስ በነበራቸው ጨዋታ ላይ የጅማው አማካይ ሙሴ ካበላ ጀርባው በፕላስተር የተለጣጠፈ መለያ ለብሶ ተመልክተነዋል። በመሆኑም ይህ ጉዳይ አሁንም ትኩረት እንደሚሻ የሚያሳይ ነበር።
በተጨማሪም በጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ አርባምንጭ ከተማን በገጠመበት ጨዋታ የሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች በሙሉ በጎፈሬ የተመረተውን የቡድኑን ሁለተኛ ቀይ መለያ የተቀሙ ሲሆን በአንፃሩ ጨዋታውን በቋሚነት የጀመረው ዮሀንስ ሱጌቦ ግን ከላይ የለበሰው መለያ ቡድኑ አምና ይጠቀምበት የነበረውን የድሮ መለያን መሆኑን ታዝበናል። የዮሐንስ መለያም ከሌሎች ተለይቶ ከጀርባው የተጫዋቹ ስም ሳይሆን “Hawassa City Fc” የሚል ፅሁፍ ሰፍሮበት ተመልክተናል።
ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በዚህ ፅሁፋችን እንዳነሳነው ተቀፅላ ስሞች እና የቁልምጫ ፅሁፎችን በመለያዎች አሁን መመልከታችን ቀጥለናል። የአሁኑ ባለተራ ደግሞ የሀዋሳ ከተማው ወንድማገኝ ማዕረግ መለያው ላይ “Wonde” በሚል መጠርያ ስሙ ተቆላምጦ ተፅፎ ተመልክተናል።
👉 በሴቶች ቡድን አባላት የሚደገፉ ቡድኖች
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በሳምንቱ መጨረሻ ጅማሮውን በሀዋሳ አድርጓል ። ውድድሩ ሀዋሳ ከተማ የከተሙት የተለያዩ ቡድኖች የወንዶች ቡድኖቻቸው ጨዋታ ሲኖራቸው በስታዲየም በመገኘት ቡድኖቻቸውን ሲያበረታቱ ተመልክተናል።
የአዲስአበባ ከተማ፣ ባህር ዳር ከተማ፣ አዳማ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ የሴቶች ቡድን አባላት እና ተጫዋቾች ቡድናቸውን በስታዲየም በመገኘት ሲያበረታቱም ታይቷል።
በተለይ የመዲናይቱ ክለብ የሆነው አዲስ አበባ ከተማ በጣም ጥቂት የሚባል ደጋፊ ካላቸው የሊጉ ክለቦች መካከል አንዱ ቢሆንም የቁጥራቸው ማነሱ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ በተወሰነ መልኩ ለመቋቋም የሴቶች ቡድን አባላት ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ነበር።
👉 የሆሳዕና ደጋፊዎች ተመልሰዋል
በውጤት መጥፋት ቀስ በቀስ በስታዲየም ቁጥራቸው ተመናምኖ የነበሩት የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊዎች ከሰሞኑ ቁጥራቸው እየጨመረ ይገኛል።
ቡድኑ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፉን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው የ9ኛ ሳምንት ጨዋታ በቁጥራቸው ከፍ ያሉ የክለቡ ደጋፊዎች ቡድናቸውን በሜዳ ሲያበረታቱ ተመልክተናል። ምልሰታቸውም በድል ታጅቦ ሀዲያ ሆሳዕና ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 በማሸነፍ የተከታታይ ድሎቹን ቁጥር ሦስት አድርሶ ከነበረበት የስጋት ወረዳ ርቆ በመቀመጥ ወደ ሊጉ ዕረፍት አምርቷል።