የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የፈፀሙት የአጋርነት ስምምነት ይፋ ሆነ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኩል ከቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር የፈፀመውን የአጋርነት ስምምነት ዛሬ ከሰዓት ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በቅርብ ጊዜያት ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ከተለያዩ ተቋማት ጋር የአጋርነት ስምምነቶችን እየፈፀመ እንደሆነ ይታወቃል። አሁን ደግሞ የፋይናንስ ተቋም ከሆነው ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር የሦስት ዓመት ስምምነት ተፈፅሟል። ይጀመራል ተብሎ ከተነገረው 43 ደቂቃዎችን ዘግይቶ በተጀመረው መርሐ-ግብር ላይ የቡና ባንክ ማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ብርሃኑ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እንዲሁም ዋና ፀሐፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን ተገኝተዋል። በቅድሚያም አቶ ኢሳይያስ ጂራ ስለ አጋርነት ስምምነቱ ተከታዩን ገለፃ አድርገዋል።

“ከቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር አብረን መስራት ከጀመርን አራት ወራት ሆኖናል። በማርኬቲንግ ዲፓርትመንታች በኩል ተንቀሳቅሰን ከተቋሙ ጋር ለመስማማት ብዙ አውርተናል። አጋርነቱ አብዛኛው በወንዶች ብሔራዊ ቡድን ላይ የሚያተኩር ነው። ብሔራዊ ቡድኑ በሚያሳየው ብቃት ላይ ተመስርቶ እያደገ የሚሄድ ነው። ለምሳሌ ብሄራዊ ቡድኑ የትኛውንም የነጥብ ጨዋታ ሲያደርግ 300 ሺ ብር ይሰጣል።
መነሻ አለው። መነሻው ግን በእነሱ እና በእኛ ውይይት የሚወሰን እና ወደ ፊት የሚገለፅ ነው።

“እንዳልኩት ስምምነታችን ከአራት ወራት በላይ ሆኖታል። የአጋርነት ብሩን ይሄንን ያህል ነው ብለን ባንጠቅስም ፌዴሬሽኑ አብረውት ከሚሰሩት አጋሮች ጋር የተመጣጠነ ገንዘብ ነው የሚከፍለው። ተቋማችን የኢትዮጵያን ስም ከፊቱ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው። ዋልያ በአመት ስፖንሰር ከሚያደርገን ጋር የሚጣጣም ገንዘብ ነው ከቡና ባንክ የምናገኘው። መነሻው ደግሞ እነሱ ይዘውት ከመጡት አዲስ ሀሳብ ጋር መወያየት ይፈልጋል። ከእነርሱ ጋር ከተፈራረምን በኋላ ብሔራዊ ቡድናችን አንድ ጨዋታ አሸንፏል። ሲያሸንፍም ሽልማት ከፍለዋል። በዚህ አጋጣሚ ቡና ባንክ ከፌዴሬሽኑ ጋር ለመስራት በመወሰኑ በጣም ነው የምናመሰግነው።” በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በመቀጠል መድረኩን የያዙት የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ብርሃኑ በስምምነቱ ዙሪያ ተጨማሪ ሀሳብ በስፍራው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ተናግረዋል።

“ቡና ባንክ የኢትዮጵያን ስም ከፍ የሚያደርጉ ሁነቶች ላይ የመሳተፍ ቁርጠኝነት አለው። አሁን ሁለተኛ ጊዜ ነው እንደዚህ አይነት ስምምነት ላይ ያገኛችሁን። ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ቡናን ስፖንሰር አድርገናል። አሁን ደግሞ ሀገርን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ተቋምን ነው ለማድረግ የመጣነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሁላችንም ወኪል ነው። ቡድኑ ደግሞ ውጤታማ እንዲሆን የገንዘብም ይሁን የትኛውንም ድጋፍ ለማድረግ ባንካችን ድጋፍ ያደርጋል። ባንካችን የባንክ አገልግሎት ነው የሚሰጠው። ከዚህ መነሻነት ፌዴሬሽኑ የሚያደርጋቸውን የባንክ አገልግሎቶች በእኛ ለማድረግ ተስማምተናል። ይህ ደግሞ አብረን ለማደግ ካለፍ ፍላጎት ነው።

“እንደተገለፀው ስምምነቱ ከተፈፀመ አራት ወራት አስቆጥሯል። ግን በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ መነሻነት አዘግይተነው ነበር። አሁን ደግሞ ቡድኑም ለአፍሪካ ዋንጫ ስለሄደ ጊዜውን መርጠናል። በስምምነቱ መሰረት ገንዘቡ ቋሚ አደለም። የሚያድግ ነው። ከውጤት ጋር ተያይዞም የሚያድግ ስለሆነ መገደቡን አልፈለግንም። ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በሚያደርጋቸው ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ላይ የቡና ባንክ አርማ አብሮ ይኖራል። እንዳልኩትም የፌዴሬሽኑ የፋይናንስ እንቅስቃሴ በእኛ በኩል ይሆናል።” በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል።

ቸርችል ጎዳና አካባቢ በሚገኘው ሞናርክ ፓርክቪው ሆቴል እየተሰጠ ያለው መግለጫ ቀጥሎ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ስምምነቱ ለሦስት ዓመት የሚቆይ ኮንትራት እንደሆነ እና በየአመቱ እንደሚታደስ ተናግረዋል።

በመጨረሻም ቀድመው የፊርማ ሥነ-ስርዓት ያከናወኑት ሁለቱ ተቋማት የአርማ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ መርሐ-ግብሩ ፍፃሜውን አግኝቷል።

ያጋሩ