“ይህን እኔ አላደረግኩም፤ ከክለቡ ጋር ተማምነን ነበር” – ናትናኤል በርሄ

ረፋድ ላይ በነበረው ዘገባችን ኢትዮጵያ ቡና ናትናኤል በርሄ ማሰናበቱን ተከትሎ በቀረበው ውሳኔ ዙርያ ተጫዋቹ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል።

ከኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ከተጫዋቾች የዲሲፕሊን መመርያ ውጭ በስፖርታዊ ውርርድ ኢትዮጵያ ቡና ይሸነፋል በማለት የእምነት ማጉዳል ፈፅሟል ያለው ናትናኤል በርሄን በዛሬው ዕለት ማሰናበቱን ረፋድ ላይ በነበረው ዘገባችን መግለፃችን ይታወሳል። ሶከር ኢትዮጵያ መረጃውን ለአንባቢዎቿ ካጋራች በኃላ ናትናኤል በርሄ በጉዳዩ ዙርያ በክለቡ ላይ ቅሬታ እንዳለው እና መናገር የምፈልገው ነገር አለ በማለት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ተከታዩን አስተያየት ከተጫዋቹ አንደበት እንደወረደ አቅርበነዋል።

” ሁኔታው ተፈጠረ በተባለበት ጊዜ ጠርተውኝ አናግሬያቸው ነበር። ከእኔ ምንም እንዳልመጣ ቁጥር ብቻ ተልኮልኝ እንጂ በራሴ የሰራሁት ነገር የለም። ቁጥር ብቻ ነው የተላከልኝ፤ ይሄን ደግሞ ሄደው ከገለልተኛ ወገን አጣርተው አረጋግጠዋል። ይህን እኔ እንዳላደረኩ ተነጋግረን ተማምነን ነው የተለያየነው። ጉዳዩን እኔ እንደማላውቅ፤ ቡና ይሸነፋል እንዳላልኩ አሰልጣኝ ካሳዬ አጠቃላይ የአሰልጣኝ አባላቱ በሙሉ በተገኙበት ተወያይተን ተማምነን ነው የተለያየነው። ስለዚህ እኔ አስቤ ያደረኩት ነገር የለም። ከዚህ በፊትም ይህን ውርርድ የምጫወተው ሌላ ሰው ቁጥር እየላከልኝ ነው። ለክለቡም በየትኛውም ሁኔታ ይህንን ነገር ፈፅሜያለው ብዬ አላመንኩም። ይህ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። እኔ ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ብቅ ካልኩ ገና አጭር የጊዜዬ ነው። ነገ ተስፋን በማደርግ ትልቅ ተጫዋችም በመሆን ሀገሬን ለማገልገል የማስብ ወጣት ተጫዋች ነኝ። በመሆንም ክለቡ የወሰነብኝ ውሳኔ ተገቢ ያልሆነ በጣም ከባድ በመሆኑ ውሳኔውን በድጋሚ እንዲመለከትልኝ እጠይቃለሁ።” ብሏል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ክለቡም ሆነ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሚያወጡት አዳዲስ ነገሮች ካሉ ተከታትለን የምናቀርብ ይሆናል።