የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት የትኩረት ነጥቦች እና ምርጥ 11

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን በመጀመሪያ ሳምንት የታዘብናቸውን ዐበይት ጉዳዮች እንዲሁም የሳምንቱን ምርጥ 11 በተከታይ መልኩ ወደ እናንተ አቅርበንላችዋል፡፡

ውድድሩ በበቂ የክብር እንግዶች አለመጀመር

የ2014 የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ ከተማ ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ በተደረጉ የአንደኛ ሳምንት ጨዋታዎች መጀመራቸው ይታወሳል። ይህ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በፌዴሬሽኑ ስር ካሉ ውድድሮች በከፍታ ቀዳሚ ቢሆንም አወዳዳሪው አካል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሰጠው ትኩረት እጅግ ያነሰ ይመስላል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን እጅጉን በደመቀ ድባብ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ዓመቱ የተጀመረ ቢሆንም ዘንድሮ ላይ በመጀመሪያ የሀዋሳ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ላይ ላይ የተቀዛቀዘ የመክፈቻ ስነ ስርአትን ታዝበናል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በመክፈቻ ጨዋታ ላይ አንድም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ አባላትም ሆነ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሳይገኙ መቅረታቸው እና ድባቡ ቀዝቃዛ መሆኑ አስገራሚ ጉዳይ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ውድድሩንም የፌድሬሽኑ የውድድር እና ስነ-ስርዓት ዳይሬክተር አቶ ከበደ ወርቁ በብቸኝነት ቀገኝተው የፕሮግራሙን አስጀምረውታል። ምንም እንኳን በዕለቱ ምሽት ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ካሜሩን ለሚያደርገው ጉዞ የሽኝት መርሐ ግብር የነበረ ቢሆንም የአየር በረራ አማራጭ በመጠቀም ወይም ሁለቱ መርሐ ግብሮች እንዳይጋጩ ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው ይገባ ነበር።

በኮቪድ የተያዙ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ስታዲየም መገኘታቸው

ከ2013 ዓ. ም ጀምሮ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ክለቦች አንድ ከተማ በመክተም የኮቪድ 19 ፕሮቶኮልን በጠበቀ መልኩ ውድድሩ በተሳካ ሁኔታ ተካሂዶ ከሞላ ጎደች መጠናቀቁ ይታወሳል።የ2014 ዓ.ም የውድድር ዘመን እንደ አምናው የኮቪድ 19 ፕሮቶኮል በጠበቀ መልኩ እንዲደረግ ቢወሰንም በአንደኛ ሳምንት ላይ የተመለከትነው ያንን የሚያሳይ አይመስልም። አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች በኮቪድ 19 ተይዘው ሳለ ከተመልካች እና ከተጫዋቾች ጋር ተቀላቅለው ጨዋታዎችን ሲመለከቱ ማየታችን እንዲሁም ደግሞ የኮቪድ 19 ቅድመ ጥንቃቄዎችን ተግባራዊ ሳይደረጉ እና ብዙ ቸልተኝነት በአወዳዳሪውም ሆነ በክለቦች መሀል እየታየ መገኘቱ አፋጣኝ ውሳኔ የሚያስፈልገው መሆኑን ለመገንዘብ ችለናል፡፡ይህ ጉዳይ በቶሎ የማይሰተካከል ከሆነ እየተስፋፋ ከሰሞኑ የመጣው የኮቪድ 19 በሽታ ውድድሩን ሊያደበዝዝ እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይመስልም፡፡

ፀሀይ እና አርቴፊሻል ሜዳ ለሴቶች… ?

የዘንድሮ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ለየት የሚያደርገው በቀን ሦስት ጨዋታዎች እየተደረጉ መሆኑ ነው። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ውድድሩ በሁለት ሜዳ እንዲደረግ ቢታሰብም የሀዋሳ ግብርና ሜዳ ለውድድር ማሟላት ያለበትን መስፈርት ባላሟሟላቱ ውድድሩ በሀዋሳ አርቴፊሻል ስታዲየም በቀን ሦስት ጨዋታዎች በሁለት ቀን እንዲደረግ የተሻሻለው ፕሮግራም ያሳያል። በስፍራው ተገኝተን እንደታዘብነው ከሆነ ግን ቀትር 5:00 ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎች ለሴቶች እጅግ አስቸጋሪ እና ለከፋ ህመም እና ጉዳት የሚያደርስ እና እያደረሰም መሆኑመታዘብ የቻልን ሲሆን አወዳዳሪው አካልም ይህንን ፕሮግራም ማስተካከያ ቢያደርግ የሚል መልዕክትን ለማስተላለፍ እንወዳለን ።

ዘንድሮ ጠንካራ ፉክክር እንደምንመለከት ፍንጭ የሰጠ ሳምንት

በ2014 የውድድር ዓመት አብዛኞቹ ክለቦች ፈጥነው ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት መግባታቸው ጠንካራ ቡድን ይዘው ይመጣሉ የሚሉ ግምቶች ቢበረክቱም ያ ሳይሆን በተቃራኒው የተወሰኑ ክለቦች በመጠኑ የተሻለ ቡድን እና የተደራጀ ነገርን በአንደኛው ሳምንት ማሳየት ችለዋል። ሆኖም ውድድሩ ገና አንደኛ ሳምንት ላይ በመገኝቱ ይህንን ማለት ቢከብድም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና ቅርፅ እንደ ቦሌ ክፍለከተማ በወጣት ተጫዋቾች ቡድኑን በመገንባት በአሰልጣኝ ቻለው ለሜቻ ማየት የቻልን ሲሆን አሰልጣኝ መሰረት ማኔ እንዲሁ ኤሌክትሪክን እንደ አዲስ በመገንባት ይዛው የመጣችው ለተጋጣሚ የሚያስቸግር እና ኳስን መሰረት ያደረገ ጠንካራ ቡድን እንደሆነ ታዝበናል። ሦስተኛው ጠንካራ ቡድን ከወዲሁ ማየት የቻልንበት አርባምንጭ ከተማ ሲሆን አዲስ የተሾመው አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ሁሌም የሚታወቅበትን ጥብቅ ቡድን በአንደኛ ሳምንት አስመልክቶናል።

ወንድ ዳኞች ከዓመታት በኋላ ወደ ሴቶች ሊግ ብቅ ብለዋል

ባለፉት ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ በሴት ዳኞች ብቻ እየተመራ የቆየ ሲሆን ዘንድሮ ግን ዳግም ከሁለት አመታት በኋላ ወንድ ዳኞችን መመልከት ችለናል፡፡ያለፉትን ሁለት አመታት ሴት ዳኞች ብቻ ሊጉን እንዲመሩት ተብሎ ተገድቦ የቆየ ሲሆን ከ2014 የውድድር ዘመን አንስቶ ግን ወንድ ዳኞች ተካተው ማጫወት ጀምረዋል፡፡ለዚህም ማሳያው ሁለት ዋና ወንድ ዳኞችን በመጀመሪያው የውድድር ሳምንት ሲመሩ አስተውለዋል፡፡

ከወዲሁ የመርሐ ግብር ቅያሪ

ሊጉ ቅዳሜ በሚደረጉ 6 ጨዋታዎች እንደሚጀመር ተገልፆ የነበረ ቢሆንም እጅግ በዘገየ ሁኔታ ዓርብ ምሽት የፕሮግራም ማሻሻያ እንዲደረግ መወሰኑ አግራሞት ያጫረ ጉዳይ ሆኗል። ውድድሩ ሊጀመር ሰዓታት ሲቀሩት አመሻሽ ላይ በተደረገ ውይይት መነሻነት በፍጥነት በሁለት ሜዳዎች ሊደረግ የነበረውን ጨዋታ አንዱ ተሰርዞ በአንደኛው ሜዳ ላይ መደረጉ ብዙም አስከፊ ባይሆንም የፕሮግራም ለውጥ የተደረገበት ጊዜ ግን መደገም የሌለበት እና አወዳዳሪውም አካል በጥንቃቄ በቀጣይ ሊያሻሽለው የሚገባ ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡

የአንደኛ ሳምንት የሶከር ኢትዮጵያ ምርጥ 11

አሰላለፍ፡ 3-4-3

ግብ ጠባቂ

ማርታ በቀለ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፋ የተጫወተችው ማርታ በግል ጉዳይ ከሜዳ ርቃ ከቆየች በኋላ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ኢትዮ ኤሌክትሪክን ተቀላቅላ ዘንድሮም በክለቡ ቆይታ እያደረገች የምትገኝ ሲሆን በዚህኛው ሳምንት ቡድኗ ተፈትኖ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲረታ በአንፃራዊነት የተሻለ ሳምንትን በማሳለፏ በቦታው ተመራጭ ሆናለች፡፡

ተከላካዮች

ምህረት ተሰማ – ሀዋሳ ከተማ

ወደ ልጅነት ክለቧ መከላከያን በመልቀቅ ዳግም መቀላቀል የቻለችሁ የመስመር ተከላካዩዋ ሀዋሳ ከተማ በመክፈቻ መርሀግብሩ ድሬዳዋ ከተማን ከጨዋታ ብልጫ ጋር መርታት ሲችል በመስመር መከላከልም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ የነበራት ሚና ላቅ ብሎ በመገኘቱ የሳምንቱ ምርጥ ስብስብ ውስጥ ልናካትታት ችለናል፡፡

ትዝታ ኃይለሚካኤል – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በወጥነት በፕሪምየር ሊጉ የመከላከል አቅማቸው ጎልቶ ከሚታዩ የመሀል ተከላካዮች መካከል ሀዋሳ ከተማን ለቃ በክረምቱ ንግድ ባንክ የደረሰችሁ ትዝታ ንግድ ባንክ ተፈትኖ አርባምንጭ ከተማን ማሸነፍ ሲችል ፈጣን የነበሩትን የአርባምንጭ አጥቂዎችን በመቆጣጠር በሜዳ ላይ ታሳይ የነበረው ድንቅ ብቃት በምርጥነት አስመርጧታል፡፡

እፀገነት ብዙነህ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የቀድሞው ክለቧ ንግድ ባንክን ዘንድሮ በድጋሚ የተቀላቀለችሁ እፀገነት ተለምዷዊ አጨዋወቷን በመጀመሪያው የሊጉ ሳምንት ላይ ማሳየት ችላለች፡፡ከመከላከሉ ይልቅ በይበልጥ ወደ ፊት ተስባ በመጫወት ለቡድኗ ውጤታማነት አስተዋጽኦ የነበራት ተጫዋቿ ያሳየችሁን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተከትሎ በቦታው ተመራጭ ልትሆን ችላለች፡፡

አማካዮች

ሰናይት ቦጋለ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በሴቶች እግር ኳስ ወጥ በሆነ አቋም ለቡድኖቻቸው የጎላ ሚናን ከሚወጡ ተጫዋቾች መካከል አማካዩዋ ሰናይት ቀዳሚዋ ተጫዋች ናት፡፡በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ንግድ ባንክን በመቀላቀል ለክለቡ ውጤታማ መሆን መቻሏ የሚታወስ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት በጀመረው እና ንግድ ባንክ አርባምንጭን በፕሪምየር ሊጉ መርታት ሲችል ወጥ የሆነ የሜዳ ላይ አቅሟን ማሳየት በመቻሏ የመጀመሪያ ሳምንት የምርጥ አማካይነት ምርጫው ላይ መካተት ችላለች፡፡

ህይወት ረጉ – ሀዋሳ ከተማ

በያዝነው ዓመት ሀዋሳን ከተቀላቀሉ ተጫዋቾች መካከል አንጋፋዋ አማካይ ህይወት ረጉ ትጠቀሳለች፡፡ መከላከያን በመልቀቅ ሀዋሳ የደረሰችሁ የከፍተኛ ልምድ ባለቤቷ ክለቧ ድሬዳዋን ረቶ አመቱን በድል ሲጀምር ለቡድኗ በዓማካይ ስፍራ ትልቁን ግልጋሎት ከመስጠቷ ባለፈ ከሦስቱ ግቦች አንዱን ከመረብ ማሳረፍ መቻሏ ተመራጭ መሆን እንድችል አድርጓታል፡፡

ኝቦኝ የን – ኢትዮ ኤሌክትሪክ

የጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ፍሬ የሆነችው እና የንግድ ባንክ የሁለት ዓመት ቆይታን በማድረግ ዘንድሮ የአልጣኝ መሠረት ማኔን ስብስብ የተቀላቀለችው ኝቦኝ ኤሌክትሪክ ተፈትኖም ቢሆን ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲያሸንፍ መሐል ሜዳውን በመቆጣጠር ረገድ በግሏ የነበራት ጉልህ ድርሻ በምርጥነት አስመርጧታል፡፡

ዙፋን ደፈርሻ – ሀዋሳ ከተማ

የሀዋሳ ከተማ የሶስተኛ ዓመት ቆይታዋን በአምበልነት በመምራት ጅምሯ ያደረገችሁ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቿ ዙፋን ቡድኗ በመክፈቻ ጨወታ 3ለ0 በሆነ ውጤት የምስራቁን ክለብ ማሸነፍ ሲችል ሜዳውን በአግባቡ በመጠቀሞ ስታደርግ የነበረበት መንገድ እና ለቡድኗም አንድ ግብ ማስቆጠር መቻሏ እንድትመረጥ አድርጓታል፡፡

አጥቂዎች

ንግስት በቀለ – ቦሌ ክፍለከተማ

ከአሰልጣኝ ቻለው ለሜቻ ጋር ተያይዛ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ቦሌ ክፍለከተማን የተቀላቀለችሁ ታዳጊዋ አጥቂ ንግስት በቀለ በመጀመሪያ ዓመት የፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎዋ ክለቧ መከላከያን ገጥሞ ምንም እንኳን ሽንፈት ቢገጥመው በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ሆና ከመታየቷ በተጨማሪ ሁለት ኳሶችን በማስቆጠር ጥሩ አጀማመርን አሳይታናለች፡፡

ሴናፍ ዋቁማ – መከላከያ

ከአዳማ ከተማ በኋላ በመከላከያ ክለብ ውስጥ ሁለተኛ አመቷ ላይ ያለችሁ ሴናፍ ከአመት አመት ከሷ የሚጠበቁ የሜዳ ላይ ቆይታን በተደጋጋሚ ስታደርግ የምትታወቅ ሲሆን ክለቧ በሳምንቱ ቦሌን 3ለ2 መርታት ሲችል ሁለት ግሩም ኳሶችን በማስቆጠር እንዲሁም ደግሞ በሜዳ ላይ አሳይታ ከነበረው እልህ አስጨራሽ እንቅስቃሴዋ አንፃር በምርጥነት አካተናል፡፡

ብሩክታዊት አየለ – አዲስ አበባ ከተማ

የቀድሞዋ የመከላከያ እና እንዲሁም በክረምቱ አዳማን ለቃ የመዲናይቱን መጠሪያ ክለብ የተቀላቀለችሁ ተጫዋቿ በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታ ምንም እንኳን እንደ አንድ አጥቂ ለክለቧ ጎል ማስቆጠር ባትችልም በሜዳ የሚታይባት ትጋት ከማጥቃቱ ረገድ በመከላከሉም የነበራት ሚና የገዘፈ መሆኑ በምርጥ 11 ስብስብ ውስጥ ከሌሎች አጥቂዎች ተሽላ በመታየቷ ተመራጭ መሆን ችላለች፡፡

ምርጥ አሰልጣኝ – መሰረት ማኔ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ውስጥ ረጅም አመታት ያሳለፈችሁ እና በአሁኑ ሰአት በኢትዮ ኤሌክትሪክ የአሰልጣኝነት መንበር ላይ የምትገኘዋ መሠረት ዘንድሮ ከኤሌክትሪክ ጋር የተለየ አቀራረብን ይዛ የመጣች ይመስላል፡፡በሊጉ የመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተፈትኖ 2ለ1 ማሸነፍ የቻለ ሲሆን ቡድኑ ለመጫወት የሚፈለገው የጨዋታ መንገድ ከአምናው በተሻለ መሆኑና አሰልጣኟም በስብስቧ ውስጥ ወጣቶች በማካተት ብቅ ማለቷ ከቦሌው አሰልጣኝ ቻለው ለሜቻ እና የአዲስ አበባዋ የሺሃረግ ለገሰ ጋር ተፎካክራ በመጨረሻም የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝነት ቦታን ልታገኝ ችላለች፡፡

ተጠባባቂ

ስርጉት ተስፋዬ – አዲስ አበባ ከተማ
እቴነሽ ደሰታ -ቅዱስ ጊዮርጊስ
አለምነሽ ገረመው – ንግድ ባንክ
ህይወት ደንጊሶ -ንግድ ባንክ
አሪያት ኦዶንግ – አዲስ አበባ ከተማ
ጋብርኤላ አበበ -ቅዱስ ጊዮርጊስ
ሄለን እሸቱ – አዳማ ከተማ

የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች (በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ)

ረቡዕ

ጌዴኦ ዲላ ከ ቦሌ ክ/ከተማ 3፡00

መከላከያ ከ አዳማ ከተማ 5፡00

አቃቂ ቃሊቲ ከ ሀዋሳ ከተማ 10፡00

ሐሙስ

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3፡00

ባህርዳር ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ 5፡00

ድሬዳዋ ከተማ ከ አዲስአበባ ከተማ 10፡00