በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንድ ተጫዋች ከስብስቡ ውጪ አድርጎ በምትኩ ለአንድ ተጫዋች ጥሪ ማቅረቡን ፌዴሬሽኑ ገልጿል።
ከአስራ አንድ ቀናት በኋላ የሚጀመረው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባሳለፍነው ሳምንት ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ በማቅረብ ከአራት ቀናት በፊት ለውድድሩ ዝግጅቱን ለማድረግ ወደ ስፍራው ማቅናቱ ይታወሳል። ያውንዴ የደረሰው ልዑኩ ልምምዱን አጠናክሮ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በቅድሚያ ጥሪ ከቀረበላቸው ተጫዋቾች መካከል የባህር ዳር ከተማው የመሐል ተከላካይ መናፍ ዐወል ግን በህመም ምክንያት ከአጋሮቹ ጋር ወደ ያውንዴ አላመራም ነበር።
ተጫዋቹ ካጋጠመው ህመም አለመዳኑን ተከትሎም ከስብስቡ ውጪ እንደተደረገ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከደቂቃዎች በፊት ይፋ አድርጓል። በእርሱ ምትክም ከዛው ከባህር ዳር በመስመር እና በመሐል ተከላካይነት የሚጫወተው አህመድ ረሺድ ጥሪ እንደደረሰው ተመላክቷል። ተጫዋቹም በነገው ዕለት ወደ ካሜሩን ያውንዴ አምርቶ የብሔራዊ ቡድን አጋሮቹን እንደሚቀላቀል ለማወቅ ተችሏል።
በተያያዘ ዜና በዴ ዱፒዮቴ ሆቴል ማረፊያውን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ልምምዱን በአክስዋን ሜዳ እያከናወነ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የአራተኛ ቀን ልምምዱን የሚያደርግ ይሆናል። ከስፍራው ባገኘነው መረጃም ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ።