​የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ነገ ስብስቡን ይቀላቀላል

ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅቱን በስፍራው እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግዙፉን አጥቂ ነገ ያገኛል።

በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለውድድሩ ጥሪ ካቀረበላቸው 28 ተጫዋቾች መካከል 25ቱን በመያዝ ያሳለፍነው እሁድ ለዝግጅት ወደ ስፍራው ማቅናቱ ይታወቃል። ያውንዴ በሚገኘው ዴ ዱፒዮቴ ሆቴል ማረፊያውን በማድረግ ልምምዱን ሲሰራ የነበረው ቡድኑም በህመም ምክንያት ይዞት ወደ ስፍራው ያላቀናውን መናፍ ዐወል በመተው ለአህመድ ረሺድ ጥሪ ያቀረበ መሆኑን ቀድመን የዘገብን ሲሆን ተጫዋቹም በነገው ዕለት ወደ ስፍራው የሚያቀና ይሆናል። ከሰዓታት በፊት ደግሞ በግብፁ አል ጉውና የሚጫወተው ሽመልስ በቀለ ስብስቡን እንደተቀላቀለ የገለፅን ሲሆን የቀረው ብቸኛው ተጫዋች ሙጂብ ቃሲም ደግሞ ነገ ወደ ካሜሩን እንደሚጓዝ ድረ-ገፃችን አውቃለች።

በአልጄሪያው ጄኤስ ካቢሌ የሚጫወተው ሙጂብ እንደ ሽመልስ አዲስ አበባ መምጣት ሳይጠበቅበት በቱርክ ኢስታምቡል አድርጎ ወደ ካሜሩን እንደሚያቀናም ለማወቅ ችለናል። ተጫዋቹ ዘግይቶ ስብስቡን በመቀላቀሉም ከነገው የሱዳን የአቋም መለኪያ ጨዋታ ውጪ እንደሆነ ተነግሯል።

ያጋሩ