ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ አቃቂ ላይ ጎል አዝንቦ አሸንፏል

Read Time:2 Minute, 3 Second

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር የሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሦስተኛ የቀኑ ጨዋታ ከሰዓት ሲቀጥል ሀዋሳ ከተማ በጎል ተንበሽብሾ አቃቂ ቃሊቲን 9 ለ 1 ረምርሟል፡፡

የዕለቱ ዋና ዳኛ ማርታ መለሰ የጨዋታውን መጀመር ካበሰረችበት ፊሽካ ጀምሮ ሀዋሳ ከተማዎች ጎል ለማስቆጠር ማነፍነፍ ጀምረዋል፡፡ በመስመር ላይ እና መሀል ሜዳ ላይ ትኩረት ባደረገ የጨዋታ መንገድ በተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫን መውሰድ የቻሉት ሀዋሳዎች ከህይወት ረጉ እና ቅድስት ቴካ ከሚመራው የመሀል ሜዳ ጥምረት በሚፈጠር የማጥቃት ሀይል በፈጣኖቹ የፊት አጥቂዎች ቱሪስት ፣ ረድኤት እና ነፃነት ታግዘው መጫወታቸውን ቀጥለው 7ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል፡፡ ቅድስት ቴካ ከግራ ባደላ አቅጣጫ የሰጠቻትን ኳስ ቱሪስት ለማ ከመረብ በማሳረፍ ክለቧን መሪ አድርጋለች፡፡ግብ ካስቆጠሩ በኋላ የአቃቂ ቃሊቲን የጨዋታ ሂደት በማፈራረስ በተደጋጋሚ ቶሎ ቶሎ ጫናዎችን ማሳደራቸውን የቀጠሉት የአሰልጣኝ መልካሙ ታፈረ ልጆች በተለይ በረድኤት ፣ ነፃነት እና ቱሪስት ያለቀላቸውን የግብ ዕድሎችን ሲያገኙ እና በቀላሉ ሲያመክኑ አስተውለናል፡፡

ይሁን እንጂ ፍፁም የአቃቂ ቃሊቲ የመከላከል አቅም ከደቂቃ ደቂቃ እየተዳከመ መምጣቱ ሀዋሳዎችን ነፃነት የሰጣቸው ይመስላል፡፡ 19ኛው ደቂቃ ላይ የአቃቂ ተከላካዮች ፍፁም ዝንጉነትን ተመልክታ በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋች የሆነችሁ ረድኤት አስረሳኸኝ ሁለተኛውን ጎል ለክለቧ በማስቆጠር የጎል መጠኑን ከፍ አድርጋለች፡፡ ሁለተኛ ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ጨዋታ ሪትም ለመግባት የሚመስል እንቅስቃሴን ለማድረግ አቃቂዎች በመጠኑም ቢሆን ጥረት አድርገዋል፡፡ በተለይ ማህሌት ኃይሉ በሀዋሳ የግራ የግብ ክልል አካባቢ ወደ ጎል በቀጥታ መታ ፍሬወይኒ ከያዘችባት በኋላ ጎል ሊያስቆጥሩ ችለዋል፡፡

በሀዋሳ የቀኝ መስመር ከሳጥን ውጪ የሚመስል ጥፋት በሀዋሳ ተከላካዮች በመፈፀሙ የዕለቱ ዳኛ አወዛጋቢ በሆነ ውሳኔ የፍፁም ቅጣት ምት በማለት መስጠቷን ተከትሎ የሀዋሳ ተጫዋቾች በዳኛዋ ማርታ መለሰ ላይ ጠንከር ያለ ተቃውሞን ማሰማት ቢችሉም የአልቢትሯ ውሳኔ ፀንቶ ትዕግስት ሽኩር ከመረብ አሳርፋው ጨዋታው ወደ 2ለ1 ተሸጋግሯል፡፡ ሆኖም ወደ መልበሻ ክፍል ቡድኖቹ ሊያመሩ በተጨማረ ደቂቃ ቅድስት ዘለቀ ለሀዋሳ ሶስተኛ ጎል በማስቆጠሯ ለእረፍት በ3ለ1 ውጤት ሊወጡ ችለዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል ሀዋሳ ከተማዎች አርባ አምስቱን ደቂቃዎች በሚባል መልኩ በአሰልጣኝ ዮናስ ቡድን ላይ ጥቃት በመሰንዘር መጓዝ የቻሉበት ነበር፡፡ከመልበሻ ቤት ከተመለሱ አራት ያህል ደቂቃ ሲቀረው ነፃነት መና ፊት ለፊት ያገኘችሁን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረችው አማካዩዋ ህይወት ረጉ ሰጥታት አንጋፋ ተጫዋቾሞ አራተኛ የሆነች የሀዋሳን ጎል ማግባት ችላለች፡፡ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ ህይወት ከሳጥን ውጪ አስደናቂ ጎል ከመረብ በማዋሃድ ሀዋሳን ወደ አምስት አሻግራለች፡፡

ለአፍታም ቢሆን ከማጥቃት ያልቦዘኑት የሀይቆቹ እንስቶች ጌዲኦ ዲላን በመልቀቅ ዘንድሮ ሀዋሳ የደረሰችው የወቅቱ ከ20 አመት ብሔራዊ ቡድን ስብስብ አባል የሆነችሁ ቱሪስት ለማ በ58ተኛው እና 73ተኛው ደቂቃ ላይ ለራሷ ሀትሪክ የሰራችበትን ክለቧን ደግሞ ሰባተኛ የጨዋታውን ጎል እንዲያገኝ አስችላለች፡፡ በአንድ ሁለት ቅብብል ለተጋጣሚያቸው ፋታ መንሳታቸውን የቀጠሉት ሀዋሳ ከተማዎች ከታዳጊ የክለቡ ቡድን የተገኙት እና ተቀይረው በገቡት እሙሽ ዳንኤል እና በረከት ጴጥሮስ ጎሎች አካዎንታቸውን አስፍተው ጨዋታውን 9ለ1 በሆነ አስገራሚ ውጤት አሸንፈው ወጥተዋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ለሀዋሳ ሶስት ጎሎችን ያስቆጠረችሁ ቱሪስት ለማ የቤቲካ የጨዋታ ምርጥነት ሽለማትን አግኝታለች፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
ያጋሩ
error: Content is protected !!