ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንግድ ባንክ እና ባህር ዳር ሶስት ነጥብ አግኝተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ሁለት መርሀግብር ረፋድ ላይ ተደረገው ኢትዮጽያ ንግድ ባንክ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 3ለ0 ባህርዳር ከተማ በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊስን 2ለ1 በመርታት ሙሉ ሦስት ነጥብ አግኝተዋል፡፡

3፡00 ሲል ብርቱ ፉክክርን ያስመለከተን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ጀምሯል፡፡ ሁለቱ አሰልጣኞች ለመጫወት ያሰቡትን የጨዋታ መንገድ ለመተግበር አለመቸገራቸውን በሚገባ ማየት በቻልንበት ጨዋታ በመጀመሪያው የጨዋታ ደቂቃዎች ንግድ ባንኮች ከመሀል ክፍሉ በቅብብሎሽ በሚፍጥሩት የጨዋታ መንገድ እና በመስመር ላይ በተሻጋሪ ኳሶች ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት ሲያደርጉ በደንብ ተስተውሏል፡፡ 9ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ግራ የኤሌክትሪክ የግብ አቅጣጫ ካደላ ቦታ ጋር የተገኘን ቅጣት ምት ሎዛ አበራ በቀጥታ ወደ ጎል ስትመታው ግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለ በሚገርም ብቃት ስትመልሰው በድጋሚ አረጋሽ ካልሳ ብታገኘውም ድንቅ የነበረችሁ ማርታ አሁንም ልታወጣባት ችላለች፡፡

ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ሎዛ ከሰናይት ቦጋለ ጋር በፈጠረችሁ ስብጥር ሰናይት ሳጥኑ ውስጥ ከግቡ ትይዩ ሆና ስትመታው ጥሩ የሜዳ ላይ አቅሟን ስታሳይ የነበረችሁ ግብ ጠባቂዋ ማርታ በሚገርም አቅሟ መልሳባታለች፡፡የአሰልጣኝ መሠረት ማኔ ቡድን የሆነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ኳስን በማንሸራሸር እና በአጥቂዎቹ ትንቢት ሳሙኤል እና አይናለም አሳምነው አማካኝነት ወደ ጎል መጠጋት ቢችሉም ጠጣር የነበረውን የንግድ ባንክ የተከላካይ ክፍል አልፎ ግብ ለማግኘት ግን አልቻሉም፡፡ይሁን እና ከኃላ የገነቡት የመከላከል አቅም ደካማ መሆኑን ተከትሎ ተከላካዩዋ መስከረም ኢሳያስ ኳስን ወደ ኃላ መልሳለሁ ባለችበት ቅፅበት መዲና ኳሱን አግኝታው ከመረብ በማሳረፍ ባንክን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች፡፡

ቡድኖች ከመልበሻ ሲመለሱ ተመጣጣኝነት ያለው የጨዋታ መንገድን መከተል ቢችሉም ከጎል አሁንም እርቅ መፈፀም የቻለው ግን ንግድ ባንክ ነበረ ማለት ይቻላል በተለይ ንግድ ባንኮች የኤሌክትሪክን የቅብብል ሂደት በማቋረጥ ወደ ፊት ሲሄዱ የነበረበት መንገድ አስገራሚ ነበረ፡፡ሎዛ አሁንም ከቅጣት ምት መታ ማርታ ካዳነችባት ሶስት ደቂቃዎች መቆጠር በኋላ 60ኛው ደቂቃ ላይ መዲና ከቀኝ ወደ ግራ መስመር አዘንብላ ላለችሁ ለአጥቂዋ ዮርዳኖስ ሰጥታት አጥቂም አስቆጠረች ተብሎ ሲጠበቅ ድንቅ የነበርቸሁ ማርታ አድናባታለች፡፡

63ኛው ደቂቃ ላይ ግን መዲና እና ሎዛ በፈጠሩት አስገራሚ የአንድ ሁለት ቅብብል በመጨረሻም የአምናዋ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሎዛ አበራ ሁለተኛ ጎል ለክለቧ ለራሷ ደግሞ የአመቱ የመጀመሪያ የጎል አካውቷን ከፍታለች፡፡አሁንም ያለ ማቋረጥ ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉት ንግድ ባንኮች ሎዛ አበራ ከሳጥን ውጪ መዲና አመቻችታ የሰጠቻትን ኳስ ከመረብ አዋህዳ ለራሷ ሁለተኛ ለክለቧ ሶስተኛ ግብ አድርጋ ጨዋታው 3ለ0 ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የቤቲካ የስፖርት ሽልማትን የንግድ ባንኳ አማካይ እመቤት አዲሱ ተሸልማለች፡፡

ሁለተኛ በነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህርዳር ከተማ ጨወታ ለአይታ ማራኪ ዕይታን ያላበሰን ነበረ፡፡በተለይ የአሰልጣኝ ራውዳ አሊ የፈረሰኞቹ እንስቶች በነፃነት ሜዳ ላይ ለመጫወት የፈለጉት ቅርፅ ያለው አጨዋወት እጅጉን አስገራሚ ነበር፡፡ለዚህም ማሳያ ጨዋታው በተጀመረ በሁለተኛ ደቂቃ በቅብብል የባህርዳር የግብ ክልል የደረሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቀኝ በኩል ፍቅርአዲስ ገዛኸኝ አሾልካ የሰጠቻትን ኳስ ቤተልሄም መንተሎ ከመረብ አሳርፋው ጊዮርጊስን መሪ ልታደርግ ችላለች፡፡

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ቢኖራቸውም የመጨረሻ ውሳኔያቸው በሂደት እየቀዘቀዘ የመጣው የሚመስሉት ቅዱስ ጊዮርጊስ በተለይ ኳስን ተቀባብለው በሚሄዱበት ወቅት ድግግሞሽ እያበዙ መሄዳቸው ለባህር ዳሮች ነፃ የጨዋታ ሚና የሰጣቸው ይመስል ነበር፡፡እቴነሽ ደስታ ከቅጣት ምት በቀጥታ መታ የባህርዳሯ ግብ ጠባቂ ሽብሬ ካንኮ ያዳነችባት ምናልበት ሁለተኛ ግብ ሊሆን የሚችል ነበር፡፡ባህርዳሮች በቤተልሄም ግዛቸው እና መንደሪን ታደሰ አማካኝነት ሙከራ ቢያደርጉም ማስቆጠር መቻል ሳይችሉ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ጨዋታው ሲጀምር በኳሱ ቁጥጥር ፍፁም በሆነ ብልጫ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ማዘውተር ቢችሉም የሚፈጥሩት ስህተት ዋና ያስከፈላቸው ይመስላል፡፡ 60ኛው ደቂቃ ላይ የቀድሞዋ የጌዲዮ ዲላ አጥቂ ሳባ ሀይለሚካኤል የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂን ስህተት በአግባቡ በመጠቀም ጎል አስቆጥራ ክለቧን 1ለ1 አድርጋለች፡፡

ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ መንደሪን ታደሰ ከርቀት ወደ ጎል ስትመታ የቅዱስ ጊዮርጊሷ ግብ ጠባቂ አይናለም ሽታ ኳሱን ያዝኩ ስትል መስመር በማለፉ በረዳት ዳኛዋ ውሳኔ ፀድቆ ጨዋታው ወደ 2ለ1 የባህርዳር መሪነት ተሸጋግሯል፡፡ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ተደጋጋሚ ጥቃትን ቅዱስ ጊዮርጊሶች መፈፀም ቢችሉም ከኃላ በተቆጠረባቸው ግቦች 2ለ1 መሸነፍ ችለዋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የቤቲካ የስፖርት ሽልማትን የቅዱስ ጊዮርጊሷ ብዙዓየው ፀጋዬ ተሸልማለች፡፡