ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የሔለን መሰለ ጎል ድሬዳዋን አሸናፊ አድርጋለች

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ስድስተኛ መርሐ-ግብር በሆነው የድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ በድሬዳዋ 1ለ0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

10፡00 ላይ የጀመረው የድሬዳዋ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ የመጀመሪያዎቹን አስር ደቂቃዎች የምስራቁ ክለብ ወደ ፊት ተስቦ በመጫወት ከተጋጣሚው ከፍ ያለ የተነሳሽነት ስሜትን ይዞ ወደ ሜዳ ሲገባ በተለይ ደግሞ ቡድኑ በመስመር አድልቶ መንቀሳቀሱ ገና በጊዜ ቀዳሚ መሆን እንዲችል አድርጎታል፡፡ በ8ተኛው ደቂቃ ላይም የቀድሞዋ የደደቢት እና መከላከያ የመስመር ተከላካይ እና በክረምቱ ድሬዳዋ የደረሰችሁ ዘቢብ ኃይለስላሴ ከቀኝ በኩል ወደ ጎል ስታሻማ የአዲስ አበባ በአዲስ አበባ ተከላካይ ተጨርፎ እንዲሁም የግብ ጠባቂዋ ስርጉት ተስፋዬ ስህተት ተጨምሮበት ሄለን መሰለ ወደ ጎልነት ለውጣው ድሬዳዋ መምራት ጀምሯል።

ድሬዳዋ ከተማዎች ግብ ካገኙ በኋላ በመልሶ ማጥቃት ታደለች አብርሃን ማዕከል ባደረገ እንቅስቃሴ ካልሆነ በስተቀር ቁጥብነት በደንብ ይታይባቸው ነበር፡፡ ወደ ጨዋታ ለመመለስ እና አቻ ለመሆን አልመው ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ጫና ማሳደርን ምርጫቸው ያደረጉት አዲስ አበባ ከተማዎች በተለይ የብሩክታዊት ፣ አሪያት እና ቤተልሄም ያለ መረጋጋት ቡይኑ ወደ አግቢነት መምጣት እንዳይችል ሲያደርጋቸው አስተውለናል፡፡በሌላ በኩል ትርሲት መገርሳ ከርቀት እና ከቅጣት ምት የምታደርጋቸው ሙከራዎቿ ግን ሻል ብለው ታይተዋል፡፡ በተለይ ትርሲት ከቀኝ በኩል መታ ተቀይራ የገባችሁ ንግስት ኃይሉ ሞክራ ለጥቂት የወጣባት ሙከራ እና ትርሲት ከሳጥን ውጪ አክርራ መትታ ተረባርበው ያወጡባት የሚያስቆጩ የመዲናይቱ ክለብ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

ከእረፍት መልስ በቀጠለው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ ተጨማሪ ጎል ለማግኘት አዲስ አበባ ከተማ በአንፃሩ ወደ አቻነት ሊያሸጋግራቸው የሚችል ግብ ፍለጋ ላይ ተጠምደው ታይተዋል፡፡ በተለይ የአሰልጣኝ የሺሃረግ ለገሰ አዲስ አበባ በሁሉም የሜዳ ክፍል ወደ ፊት በሚጣሉ ኳሶች አጋጣሚዎችን ለማግኘት ታትሯል። ይሁን እንጂ ሁለተኛ ረዳት ሆና ጨዋታውን ስትመራ የነበረችው ሱላማጢስ ኪሮስ በግልፅ የሚታዩ እና ከጨዋታ ውጪ ያልሆኑ ኳሶችኝ በተደጋጋሚ ስታስቆም መታየቱ አግራሞት የሚያጭር እንዲሁም ለቀጣዩ ሊስተካከል የሚገባው ጉዳይ መሆኑንም ታዝበናል፡፡

62ኛው ደቂቃ ላይ የአዲስ አበባዋ አማካይ ትርሲት መገርሳ በምትታወቅበት ጠንካራ ምት ከቅጣት ምት ወደ ጎል ስትመታ እና ኳሱ ብረት ገጭቶ ሲመለስ በድጋሚ ብሩክታዊት ጋር ከመድረሱ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውታል፡፡

በድሬዳዋ በኩል በአንፃሩ ታደለች አብርሃ መታ ግብ ጠባቂዋ ስርጉት እንደምንም ስትመልስ በድጋሚ ቤዛዊት አግኝታው ግብ ጠባቂዋ ስትተፋው ከሳጥን ጠርዝ ትሁን አየለ ወደ ጎል መታ ስርጉት በድጋሚ ይዛባቸዋለች፡፡ ሰናይት ባሩዳ ከርቀት ከሞከረችው ሙከራ ውጪ የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች በፍፁም የበላይነት መንቀሳቀስ የቻሉት አዲስ አበባ ከተማዎች ቶሎ ቶሎ ወደ ድሬዳዋ የግብ ክልል እየደረሱ ያገኟቸዋቸውን ግልፅ ዕድሎች ሲጠቀሙ አላስተዋልንም። በተለይ በመጨረሻው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ ትርሲት ከቅጣት ምት ሞክራ በግብ ጠባቂዋ አበባየው ሲመለስ አጥቂዎቹ ላይ ንቃት መታየት ባለቻሉ የመከነችሁ ኳስ አስቆጪዋ አጋጣሚ ነበር። በቀሪ ደቂቃ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በድሬዳዋ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የቤቲካ የጨዋታ ኮከብ ሽልማትን የድሬዳዋ ከተማዋ ዘቢብ ኃይለስላሴ አግኝታለች፡፡