የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው ሲምፖዚየም ዛሬ ተከናውኗል

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ነገ ከመደረጉ በፊት ዛሬ ሲምፖዚየም አካሂዷል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በነገው ዕለት ከመከናወኑ በፊት በዛሬው ዕለት ከማለዳ ጀምሮ አርባምንጭ በሚገኘው ሀይሌ ሪዞርት ሲምፖዚየም ተደርጓል፡፡ በጋሞ አባቶች ምርቃት እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ የመክፈቻ ንግግር የተጀመረው ሲምፖዚየሙ በመቀጠል የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ስኬት ፣ ተግዳሮት እና መፍትሔ ዙሪያ ባለሙያዎች ያጠኑትን ሀሳብ መሠረት በማድረግ ለጉባኤው አካላት አቅርበዋል። የቀረበውን ጥናታዊ ፅሁፍ ተከትሎ የፕሪምየር ሊግ ፣ የከፍተኛ ሊግ እና የአንደኛ ሊግ እንዲሁም በዕለቱ ተሳታፊ የነበሩ አካላትን ባቀፈ መልኩ ለአራት የተከፈለ ቡድን በአቶ ቴዎድሮስ የቀረበውን ሀሳብ ተንተርሶ ውይይት ተደርጓል። ተወያዮቹ ያነሱትን ሀሳብም በጋራ ለታዳሚው በተወካዮቻቸው አማካኝነት አቅርበዋል፡፡

በዋናነት ታዳጊ ፕሮጀክት ላይ በይበልጥ መሰራት አለበት ፣ የሙያ ማሻሻያ ስልጠናዎች በየጊዜው መሰጠት አለበት እንዲሁም ፌድሬሽኑ በአደረጃጀት የተሻለ ቢሆንም ይበልጥ ሊዘምን ይገባዋል ያሉ ሲሆን ክለቦችን በወቀሰው የተወያዮች ሀሳቦች ደግሞ ክለቦች ለቡድኖቻቸው ቆም ብለው ጥናት በማጥናት ዘመኑን በዋጀ መልኩ አሰራራቸውን ሊያሻሽሉ ይገባል በማለት በገለፃቸው ሲጠቁሙ ፌድሬሽኑ ከካፍ የወረደለትን የክለብ ላይሰንሲንግ መመሪያን ክለቦች በሚገባ ሊተገብሩት ይገባልም ይሄም በእቅድ እንዲመሩ ያደርጋል ሲሉም የቡድን ተወያዮች ሀሳብ አቅርበዋል። በተጨማሪነትም የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ክለብን ማሰብ የለባቸውም በሌላ በኩል ደግሞ ክለብ የያዙ አሰልጣኞች ለብሔራዊ ቡድን መመረጥም የለባቸውም የሚሉት ዋና ዋና ሀሳቦች ናቸው፡፡

የዳኞች የአቅም ውስንነት መሻሻል እንደዳለበት ፣ በከፍተኛ ሊጉ እና በአንደኛ ሊጉ ላይ የክትትል ጉድለቶች ስለ መኖራቸው እና በማርኬቲንጉ ላይ ልክ እንደ ፕሪምየር ሊጉ ሊሰራ እንደሚገባውም እና የሚዲያ አካላትም ትኩረት ሰጥተው ሊዘግቡት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ በመጨረሻም ፌድሬሽኑ የመዝገብ ቤት አሰራሩ ስለ መሻሻሉ ፣ የካፍ አካዳሚን በአግባቡ በስራ ላይ ማዋሉ እና የሰው ሀይልን ባጠናከረ መልኩ ቢሮውን ማደራጀቱን በማድነቅ ወደ ምሳ እረፍት ፕሮግራሙ አምርቷል፡፡

በአራት ተከፍሎ ከተካሄደው የቡድን ውይይት በርካታ ጠቃሚ ሀሳቦች ይሰነዘራሉ ተብሎ ቢጠበቅም አብዛኛዎቹ ያነሱት ግን ተመሳሳይነት ያለው እና ከቀረበው ፅሁፍ አንፃር ደካማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከምሳ እረፍት መልስ ውይይቱ ሲቀጥል አቶ ኢሳይያስ ጅራ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች የሲምፖዚየሙን የማጠቃለያ ንግግር አድርገዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ሁሉም የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች የሴት እንዲሁም ደግሞ ከ20 አመት በታች ቡድኖችን ከቀጣዩ አመት ጀምሮ መያዝ አለባቸው ሲሉ ሲደመጡ ይሄንንም በግዴታ ለማድረግ ከሊግ ካምፓኒው ጋር ንግግር ስለ ማድረጋቸው የገለፁ ሲሆን ሁሉም ክለቦች ለዚህ የቤት ስራውን ሊሰራ ይገባልም ብለዋል። እንደ ፌድሬሽን በሁሉም ረገድ ውጤት ለማምጣት እየተሰራ ነው ያሉት አቶ አሳይያስ ከዚህ በላይ ከተሰራም ይበልጥ ውጤታማ መሆን ይቻላልም ብለዋል፡፡ በይበልጥ ደግሞ በቡድን ተከፍሎ በነበረው ውይይት ክለቦች ያቀረቡትን ዝርዝር ሀሳቦች ፕሬዝዳንቱ ለማስረዳት የሞከሩ ሲሆን ክለቦች ከቀጣዩ አመት ጀምሮ የኦዲት ሪፖርት ካላመጡ መመዝገብ እንደማይችሉም ጭምር ከገለፁ በኋላ በብሔር ስያሜ የሚጠሩ ክለቦች ከቀጣይ አመት ጀምሮ ስሞቻቸውን ማስተካከል ይኖርባቸዋል በማለት ጠንከር ባለ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡

ከፕሬዚዳንቱ ንግግር በኋላ የዛሬው ሲምፖዚየም ማሳረጊያ የሆነ በሁለት ዙር የተካሄደ የእግርኳስ ጨዋታ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ አባያ ካምፓስ ተደርጎ በመጨረሻም በተደረገው ጨዋታ አሸናፊ የሆኑ ቡድኖች የዋንጫ እና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸው የዛሬው መርሀግብር ተደምድሟል፡፡

በነገው ዕለትም ዋናው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የሚደረግ ይሆናል።