የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ – የሁለተኛ ሳምንት የትኩረት ነጥቦች እና ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ2014 የሁለተኛ ሳምንት ትኩረት የሳቡ አበይት ነጥቦችን እና ምርጥ 11 እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል፡፡

👉ሎዛ አበራ የግብ አካውንቷን ከፍታለች

የ2013 የውድድር ዘመን ከክለቧ ንግድ ባንክ ጋር የሊጉን ዋንጫ በማንሳት እና የውድድሩ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀችው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል ሎዛ አበራ በመጀመሪያው ሳምንት ሳታስቆጥር ብትወጣም በሁለተኛው ሳምንት ወደ ግብ መመለስ ችላለች፡፡ በሁለተኛው ሳምንት የጨዋታ መርሀግብር ንግድ ባንክ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 3-0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ሁለት ጎል በማስቆጠር የግብ አካውቷን ከፍታለች።

👉ቱሪስት ለማ – የመጀመሪያዋ ሐት ትሪክ ሰሪዋ ተጫዋች

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ከጌዴኦ ዲላ ወደ ሀዋሳ ከተማ በክረምቱ ያመራችው ቱሪስት ለማ የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ1014 ዓ.ም የውድድር ዓመት የመጀመሪያውን ሐት ትሪክ መስራት ችላለች። ቱሪስት ለማ የኢትዮጵያ የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተካታ ከክለቧ ጋር ዝግጅት ማድረግ ባትችልም በውድድሩ የመጀመሪያውን ሐት ትሪክ ከመስራት አላገዳትም።

👉ሀዋሳ ከተማ በጎል የተንበሸበሸበት ሳምንት…

በሁለተኛው ሳምንት አነጋጋሪው የሆነው የሀዋሳ ከተማ እና የአቃቂ ቃሊቲ ጨዋታ ከፍተኛ ግብ የተቆጠረበት እና የጨዋታ ብልጫን ያየንበት ነበር። በዘንድሮ የውድድር አመት ቡድኑን እንደ አዲስ የተገነባው የአሰልጣኝ መልካሙ ታፈረው ሀዋሳ ከተማ ጥልቅ የተጫዋች ጥራት በየክፍሉ የያዘ ሲሆን ልምድ ያላቸውን ካደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ድሬደዋን 4ለ2 እንዲሁም አቃቂ ቃሊቲን 9-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ተጋጣሚው ላይ በአጠቃላይ 13 ግቦችን በማስቆጠር የደረጃ ሰንጠረዡን በስድስት ነጥብ እና በአስራአንድ ንፁ ግብ ክፍያ እየመራ ይገኛል። በሁለተኛው ሳምንት እጅግ አስደናቂ አቋሙን ያሳየን ሀዋሳ ከተማ በሦስተኛ ሳምንት መከላከያን የሚገጥም ሲሆን ጠንካራ ፍክክርም ይጠብቀዋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

👉የኮቪድ 19 ጥንቃቄ አሁንም ትኩረት ተነፍጎታል…

በአንደኛ ሳምንት አበይት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገን ካቀረብናቸው የኮቪድ 19 የጥንቃቄ ጉዳይ ላይ ትኩረት እንዲደረግ ጠቁመን ነበር። ሆኖም በሁለተኛው ሳምንት ይህ ነገር ሳይስተካከል ድርጊቱ ከመጀመሪያ ሳምንት በባሰ መልኩ በኮቪድ የተጠቁ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ራሳቸውን ማግለል ቢገባቸውም ከተመልካች ጋር ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ከተመልካች ጋር ተቀላቅለው ያለ ማስክ ጨዋታዎችን ሲመለከቱ ታዝበናል አወዳዳሪውም አካል ሆነ ክለቦች ይህ ጉዳይ ወደ ከፋ ደረጃ ሳይደርስ ከወዲሁ መፍትሄ ቢፈለጉለት በድጋሚ ለማስገንዘብ እንወዳለን።

👉የአወዳዳሪ ኮሚቴ አባላት ማነስ...

በሀዋሳ ከተማ እየተደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ጉድለት እያስተናገደ ወደ ሦስተኛ ሳምንት ተሸጋግሯል። የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በውድድር እና ስነ-ስርዓት ኮሜቴ እና በሴቶች ልማት ቢመራም በቂ የሰው ኃይል ኖሮ እና ውድድሩን የሚያስተባብሩ አካላት ከአምናው ባነሰ ቁጥር መመልከታችን ሌላኛው አስገራሚ ጉዳይ ነበር፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በርከት ያሉ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ውድድሩን በአግባቡ ሲመሩ የታየ ሲሆን ዘንድሮ ግን ውድድሩን የሚመሩ ኮሚቴዎች ቁጥር ማነስ አሳሳቢ ይመስላል፡፡ የኮሚቴዎች ቁጥር ያነሰ መሆኑ ደግሞ ተደጋጋሚ ችግሮች በቶሎ መፍትሄ ማግኝት እንዳይችሉ ያደረገ ሲሆን ውድድሩም በውድድር እና ስነ-ስርዓት ኦፊሰር በሆነችው ምህረት ጉታ ብቸኝነት መመራቱም ለዚህ ማሳያ ይመስላል፡፡

👉የአዳማ ከተማ ትጥቅ …

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ከአስደነቀን እና ካስመሰገነን ነገሮች ክለቦች የራሳቸውን መለያ በራሳቸው ቀለም እና ማንነት መቅረባቸው አስደሳች ቢሆንም በሁለተኛ ሳምንት ከታዘብናቸው መካከል የአዳማ ከተማ የተጫዋቾች የማሊያ ላይ ቁጥር ሊጉን በማይመጥን መልኩ በብዕር የተጻፈ እና ቁጥሮቹን መለየት በሚያስቸግር ሁኔታ ወደ ሜዳ ገብተው ሲጫወቱ አስተውለናል። የእለቱም ዳኞች ይህንን ፈቅደው ወደ ሜዳ ማስገባታቸው እንደ አንድ ትልቅ ሊግ ትኩረት ስለ መነፈጉ ማሳያ መስሏል።

የሁለተኛ ሳምንት ምርጥ 11

አሰላለፍ፡ 3-4-3

ግብ ጠባቂ

ታሪኳ በርገና – ንግድ ባንክ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቋሚ ግብ ጠባቂ እና በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በከፍተኛ የደሞዝ ዝውውር ከመከላከያ ንግድ ባንክን በመቀላቀል የሴካፋ የክለቦች ውድድር ላይ ድንቅ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻላችው ታሪኳ በያዝነው የውድድር ዓመትም ምንም ግብ ያልተቆጠረባት ግብ ጠባቂ ከመሆኗ ባለፈ በሁለተኛው ሳምንት ቡድኗ ኤሌክትሪክን ባሸነፈበት ጨዋታ የተሻለ እንቅስቃሴን ማድረግ በመቻሏ በምርጥነት ተካታለች፡፡

ተከላካዮች

ቅድስት ዘለቀ – ሀዋሳ ከተማ

ተከላካዩዋ ሀዋሳ ከተማ በከፍተኛ የግብ ልዩነት ባሸነፈበት የአቃቂው ጨዋታ ክለቧ ጨዋታውን ከተሻለ ብልጫ ጋር መርታት ሲችል በመከላከልም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ ጠንካራ ከመሆኗ አንፃር እና አንድ ግብ በማስቆጠሯ የነበራት ሚናም ላቅ ብሎ በመገኘቱ የሳምንቱ ምርጥ ስብስብ ውስጥ ልናካትታት ችለናል፡፡

ሀሰቤ ሙሶ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በወጥነት በፕሪምየር ሊጉ የመከላከል አቅማቸው ጎልቶ ከሚታዩ የመሀል ተከላካዮች መካከል ድሬደዋ ከተማን ለቃ በክረምቱ ንግድ ባንክን የተቀላቀለችው ሀሰቤ ሙሶ ንግድ ባንክ ኢትዮኤሌክትሪክን ባሸነፈበት ጨዋታ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠር በሜዳ ላይ ታሳይ የነበረው ድንቅ ብቃት በምርጥነት አስመርጧታል፡፡

ዘቢብ ኃይለስላሴ – ድሬደዋ ከተማ

በመከላከያ ብዙም የመሰለፍ እድል ያላገኘችው ዘቢብ ሀይለስላሴ ወደ ድሬዳዋ በማቅናት በሁለተኛው ሳምንት በቀኝ መስመር ከመከላከሉ ይልቅ በይበልጥ ወደ ፊት ተስባ በመጫወት ቡድኗ ከአዲስ አበባ ጋር በጠባብ ውጤት ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ለቡድኗ ውጤታማነት አስተዋጽኦ የነበራት ተጫዋቿ ያሳየችሁን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተከትሎ በቦታው ተመራጭ ልትሆን ችላለች፡፡

አማካዮች

ሰናይት ቦጋለ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በሁለተኛ ሳምንት በድጋሚ ድንቅ ብቃቷን እያሳየች የምትገኛው የንግድ ባንኳ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአማካኝ ክፍል ተጫዋች ሰናይት ቦጋለ በሁለተኛ ሳምንትም ጨዋታ ቡድኗ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባደረገው ጨዋታ ባሳየችው ወጥ አቋም ምርጫው ላይ መካተት ችላለች፡፡

ህይወት ረጉ – ሀዋሳ ከተማ

በሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያውን ሳምንት ብቃቷን መድገም የቻለችው እና ቡድኗ ከአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ላይ አስገላሚ የሆኑ ሁለት ግቦች ከግብ ክልል ውጪ ማስቆጠር ችላለች ። በጨዋታውም ባሳየችው ድንቅ እንቅስቃሴ ምርጫው ላይ መካተት ችላለች።

ገነት ኃይሉ – መከላከያ

በመከላከያ በወጥ አቋም ድንቅ እንቅስቃሴ እያሳዩ ከሚገኘ ተጫዋች መካከል አንዷ ገነት ስትሆን መከላከያ በሁለተኛ ሳምንት ከአዳም ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ያለግብ በአቻ ውጤት ቢጠናቀቅም የመሀል ሜዳውን ባላንስ በመጠበቅ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ችላለች።

እመቤት አዲሱ – ኢትዮጵዬ ንግድ ባንክ

በሳምንቱ ንግድ ባንክ ድል ሲቀናው በመሀል ሜዳው ላይ ተፅዕኖ ፈጥረው ከታዩ አመካዮች መካከል አንዷ እመቤት አዲሱ ነች፡፡ በክለቧ መለያ በመሀል ሜዳው ላይ ተፅእኖ በመፍጠር እና ለግብ የሆኑ ኳሶችን በማቀበል ተጫዋቿ ማሳየት በቻለችሁ ምርጥ ብቃት በሳምንት ቋሚ አሰላለፍ መካተት እንድትችል አድርጋለች፡፡

አጥቂዎች

ንግስት በቀለ – ቦሌ ክፍለከተማ

ወጣቷ የቦሌ ክ/ከተማ የፊት መስመር ተጫዋቿ ንግስት በቀለ ልክ እንደ አንደኛ ሳምንቱ በድንቅ ብቃቷ ግብ በማስቆጠር ቀጥላለች ።የሊጉን የመጀመሪ ጨዋታውን ካደረገው ጌዴኦ ዲላ ጋር ባደረገው ጨዋታ ቦሌ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ሁለት ግብ በማስቆጠር ከፍተኛውን ድርሻ መወጣት ችላለች።

ሎዛ አበራ – ንግድ ባንክ

የግብ አካውንቷን በሁለተኛ ሳምንት መክፈት የቻለችው ሎዛ አበራ ኤትዮ ኤሌክትሪክ 3ለ0 መርታት ሲችል ሁለት ግሩም ኳሶችን በማስቆጠር እንዲሁም ግብ የሚሆኑ ኳሶች በማቀበል ባሳየችው እንቅስቃሴ አንፃር በምርጥነት አካተናል፡፡

ቱሪስት ለማ – ሀዋሳ ከተማ

የቀድሞዋ የጌዴኦ ዲላ ተጫዋች የአሁኗ የሀዋሳ ከተማ የፊት መስመር ተጫዋቿ ቱሪስት ለማ በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታ ላይ ምንም ግብ ማስቆጠር ባትችልም ያንን የሚያካክስ በሁለተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያውን ሐት ትሪክ መስራት ችላለች። ስብስብ ውስጥ ከሌሎች አጥቂዎች ተሽላ በመታየቷ ተመራጭ መሆን ችላለች፡፡

የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ – መልካሙ ታፈረ

ሀዋሳ ከተማ በሁለተኛው ሳምንት አቃቂ ቃሊቲን 9 ግቦችን አስቆጥሮ መርታት ሲችል የአሰልጣኝ መልካሙ ታፈረው ክለብ ተጠቃሹ ነው፡፡ጠንካራ እና የተሻለ የማጥቃት አማራጭን ክለቡ ይዞ በሁለተኛው ሳምንት ሀዋሳ ማሳያቱን ተከትሎ አሰልጣኙ በሳምንቱ ምርጥነት እንዲመረጥ አስችሎታል፡፡

ተጠባባቂዎች

ስርጉት ተስፋዬ – አዲስ አበባ ከተማ
ናርዶስ ጌትነት – አዳማ ከተማ
እፀገነት ብዙነህ – ንግድ ባንክ
ትርሲት መገርሳ – አዲስ አበባ ከተማ
ረድኤት አስረሳኸኝ – ሀዋሳ ከተማ
ሔለን መሰለ – ድሬዳዋ ከተማ
ቤተልሄም መንተሎ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

የ3ኛ ሳምንት መርሐ ግብር

እሁድ ታህሳስ 24

3፡00 ሀዋሳ ከተማ ከ መከላከያ
5፡00 አዲስ አበባ ከተማ ከ አቃቂ ቃሊቲ
10፡00 አዳማ ከተማ ከ ጌዴኦ ዲላ

ሰኞ ታህሳስ 25

3፡00 ኢትዮጵያ ንግድ ባክ ከ ባህር ዳር ከተማ
5፡00 አርባምንጭ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌከትሪክ
10፡00 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ድሬዳዋ ከተማ