የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሦስተኛ ሳምንት ስድስት ጨዋታዎች ትላንት እና ዛሬ የተካሄዱ ሲሆን ንግድ ባንክ ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲያሸንፉ ቀሪዎቹ ሦስት መርሐግብሮች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ሆነዋል፡፡
ሀዋሳ ከተማ 0-0 መከላከያ
ትላንት ከተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች መካከል ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ የተጠበቀው የሀዋሳ ከተማ እና መከላከያ ጨዋታ ነበር፡፡ 3፡00 ሲል የጀመረው ይህ ጨዋታ ከመጀመሩ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ጎል ለመድረስ የሚደርጉት ጥረት በአጨራረስ ድክመት በተደጋጋሚ ሲባክን ተስተውሏል፡፡ መከላከያዎች ካለፉት ሁለት ጨዋታዎቻቸው በተለየ ኃይል የተቀላቀለበትን ጨዋታ ሲጫወቱ ለማየት ችለናል በዚህም የተነሳ ጨዋታው አሰልቺ ይዘት እንዲላበስ ሆኗል። 21ኛው ደቂቃ ላይ ነፃነት መና ቅላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ቅጣት ምት የሀዋሳ ከተማዋ አምበል ዙፋን ደፈርሻ በቀጥታ ወደ ጎል መታው ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶባታል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ከስእረፍት ሲመለሱ አሁንም ጫና ማድረጋቸውን የቀጠሉት እና በጨዋታ የተሻለ መሆን የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች ናቸው፡፡ ነፃነት መና በግራ እግሯ ከርቀት አክርራ የመታችው ኳስ የመከላከያዋ ግብ ጠባቂ እንደምንም ወደ ውጪ ያወጣችባት ሌላኛዋ በዚህኛው አጋማሽ ቀዳሚ ሙከራ ነበረች። መከላከያዎች ኃይል በቀላቀለ አጨዋወታቸው ቀጥለው በመሳይ ተመስገን እና በሴናፍ ዋቁማ አማካኝነት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ጎል ማስቆጠር ግን አልቻሉም። በተመሳሳይ የሀዋሳዋ ረድኤት አስረሳኸኝ ከርቀት አክርራ የመታችው ኳስ በመከላከያ ግብ ጠባቂ ተመልሶባታል። ሴናፍ ዋቁማ ከመሳይ ተመስገን የተሰጣትን ኳስ ይዛ ገብታ ከግብ ጠባቂዋ ጋር ለብቻዋ ተገናኝታ ለማለፍ ስትሞክር የሀዋሳ ግብ ጠባቂ መልሳባታለች የተመለሰውን ኳስ መልሳ ያገኘችው ሴናፍ ለመሳይ ተመስገን ለማቀበል ስትሞክር የሀዋሳ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውት ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል፡፡
ያለ ግብ ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የሀዋሳ ከተማዋ አማካይ እታለም አመኑ የቤቲካ የጨዋታው ኮከብ በመሆን የተዘጋጀላትን ዋንጫ ወስዳለች፡፡
አዲስ አበባ ከተማ 1-1 አቃቂ ቃሊቲ
በመቀጠል ትላንት 5፡00 ላይ የተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ ጨዋታ ነበር፡፡በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የአዲስ አበባዋ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች አርያት ኦዶንግ ከቤተልሔም ሰማን ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ይዘው ገብተው አርያት ስትሞክረ የአቃቂ ግብ ጠባቂ በሚገርም ሁኔታ የመለሰችው ኳስ የጨዋታውን ሁነት ቀይሮታል። አስረኛው ደቂቃ ላይ በሻዱ ረጋሳ ያሻማችውን ኳስ የአቃቂ ተከላካዮች መዘናጋትን ተጠቅማ አዲስ አበባን መሪ ያደረገች ጎል ቤተልሔም ሰማን አስገኝታለች፡፡ ከጎሉ መቆጠር በኋላ አዲስ አበባ ከተማዎች በአርያት አማካይነት በተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የአቃቂ ግብ ጠባቂ እስራኤል ከተማ ሙከራዎችን በሚገርም ብቃት ስትመልስባቸው ነበር። አቃቂዎች ያገኙትን የማዕዘን ኳስ የአዲስ አበባ ግብ ጠባቂ ቤተልሔም ዮሐንስ ብታወጣውም ቅርብ የነበረችው በሬዱ በቀለ በቀላሉ ወደ ጎልነት ቀይራው ቡድኗን አቻ አድርጋ ወደ መልበሻ ክፍል አምርዋል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል አዲስ አበባ ከተማዎች በይበልጥ ጫና ፈጥረው በመጫወት ግብ ለማግኘት የጣሩ ሲሆን በተለይ በአርያት አማካይነት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርጉም በዕለቱ ኮከብ የነበረችው የአቃቂ ግብ ጠባቂ እስራኤል ስታመክንባቸው ነበር።በጨዋታውም ከአስር በላይ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን ያዳነችው ግብ ጠባቂዋ ጨዋታውን ሊከታተል ከመጣ ተመልካች አድናቆት ተችሯታል ።
1-1 ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ግብ ጠባቂዋ እስራኤል ከተማ ከቤቲካ የተዘጋጀላትን የጨዋታ ምርጥነት ሽልማት ተቀብላለች፡፡
አዳማ ከተማ 1-1 ጌዲኦ ዲላ
10፡00 ሰዓት ላይ በጀመረው የአዳማ እና የጌዲዮ ዲላ ጨዋታ የመጀመሪያዎቹን ሠላሳ ደቂቃዎች አዳማ ከተማ በተሻለ አቅም በሜዳ ላይ መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ በእነኚህም ደቂቃዎች አምበሏ ናርዶስ ጌትነት ለሰርካዲስ ጉታ ከቀኝ መስመር አመቻችታ አቀብላት ሰርካዲስ ካመከነችው ኳስ በቀር ግን በጨዋታው ትኩረት ሊስብ የሚችል አጋጣሚዎችን መመልከት አልቻልንም፡፡ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ግብ ክልል በፍጥነት ቢደርሱም የአጨራረስ ችግር በጉልህ ይታይባቸው ነበር። ይሁን እና ግን 41ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ የመስመር አጥቂዋ ሰርካዲስ ጉታ ወደ ጎልነት ቀይራው አዳማን መሪ አድርጋለች፡፡
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ቀጥሎ ተቀይራ የገባችው የጌዲኦ ዲላዋ ጤናዬ ወመሴ በተደጋጋሚ የአዳማ ተከላካዮችን በማለፍ ተሻጋሪ ኳሶችን ለአጥቂዎች በመጣል ወደ አቻነት ለመመለስ ጥረት ማድረግ ጀምረዋል፡፡ የአዳማ ከተማ ግብ ጠባቂ እና ተከላካዮች ተረባርበው ያዳኑት ሌላኛው ሙከራ ነበር። ጌዲኦ ዲላዎች ጥቃት መሰንዘራቸውን ቀጥለው 67ኛው ደቂቃ ላይ ይታገሱ ተገኝወርቅ የአዳማ ተከላካዮችን በማለፍ ወደ ቀድሞ ክለቧ ለተመለሰችው አጥቂዋ አቀብላት ቤተል ጢባ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይራው ቡድኗን 1-1 አድርጋለች።
ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ አዳማ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ በተደጋጋሚ የጌዲኦ ዲላን የግብ ክልል ቢፈትሹም በተደጋጋሚ ለአጥቂዎች የሚላኩ ኳሶች ይቋረጡ ስለነበር ተጨማሪ ግቦችን መመልከት አልቻልንም። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጭማሪ ደቂቃ ላይ የአዳማዋ ተጫዋች ሄለን እሸቱ በጌዲኦ ዲላዋ መታሰቢያ ክፍሌ ላይ በሰራችው አደገኛ ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዳ ጨዋው 1-1 በሆነ ውጤት ቡድኖቹን አቻ አድርጎ ተጠናቋል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የጌዲኦ ዲላዋ አልማዝ ኪዳኔ የቤቲካ የጨዋታ ኮከብ ሽልማት ክብርን አግኝታለች፡፡
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 5-0 ባህር ዳር ከተማ
ዛሬ በሁለተኛ ቀኑ የሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቀጥለው መደረግ ሲችሉ ረፋድ 3፡00 ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ባህርዳር ከተማ ጨዋታ ቀዳሚው ነበር፡፡ የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ቡድን ንግድ ባንክ የበላይ ሆኖ በዋለበት ጨዋታ ቡድኑ በዘጠና ደቂቃው የጨዋታ ብልጫን በርከት ካሉ ጎሎች ጋር ያስመከተን ነበር፡፡ አርባ ያህል ደቂቃዎችን ያለ ጎል የተጓዘው እና ንግድ ባንኮች በተደጋጋሚ ወደ ግብ እየደረሱ በባህር ዳር የተከላካይ መስመር እስከ ተጠቀሰው ደቂቃ ድረስ መመከት ቢችልም 41ኛው ደቂቃ ላይ አለምነሽ ገመረው ከመስመር ያሻገረችላት ኳስ ተጠቅማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ንግድ ባንክ የደረሰችው ዮርዳኖስ ምዑዝ ወደ ጎልነት በመቀየር ባንክን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡
ጎል ካስተናገዱ በኋላ መረጋጋት የተሳናቸው ባህር ዳር ከተማዎች በዕለቱ ዳኛ በተሰጠው አጨቃጫቂ የፍፁም ቅጣት ምት መነሻነት በድጋሚ ግብ ተቆጥሮባቸዋል፡፡ ሎዛ አበራ 44ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረችዋ ተጫዋች ነች፡፡ መደበኛው አርባ አምስት ተጠናቆ በተሰጠው የጭማሪ ደቂቃ ላይ ከግምት 25 ሜትር ርቀት የተሰጠውን የቅጣት ምት ሎዛ አበራ ወደ ጎሎነት ለውጣው በንግድ ባንክ 3-0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
ጨዋታው ከዕረፍት መልስም በንግድ ባንክ የበላይነት የቀጠለ ሲሆን የአሰልጣኝ ሰርካአዲስ እውነቱው ባህር ዳር ከተማ ሊዲያ ጌትነት ከምታሳየው የሜዳ ላይ መልካም እንቅስቃሴ ውጪ ሲበለጥ ተስተውሏል፡፡ ነገር ግን ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ የተሻለ መሆን የቻለ ቢመስልም በመረጋጋት ክፍተት ተጨማሪ ግብ ከመረብ ላይ እንዲያርፍባቸው ሆኗል፡፡ በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ስትሆን የታየችሁ መዲና ዐወል የሰጠቻትን ግሩም ኳስ ከጎል ጋር ያዋሀደችሁ አረጋሽ ካልሳ በድንቅ አጨራረስ ነበር፡፡
ጨዋታው ሊጠናቀቅ አራት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት ሎዛ አበራ ከአረጋሽ ያገኘችሁን ተሻጋሪ ኳስ በማስቆጠር በዓመቱ ለራሷ እና ለከክለቧ አምስተኛ በጨዋታው ሐት-ትሪክ የሰራችበትን ጎል አስቆጥራ ጨዋታው 5-0 በሆነ የንግድ ባንክ አሸናፊነት ተፈፅሟል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሎዛ አበራ የቤቲካ የጨዋታ ሽልማትን አግኝታለች፡፡
አርባምንጭ ከተማ 1-0 ኢትዮ ኤሌክትሪክ
5፡00 ሲል የዛሬው ሁለተኛ የሳምንቱ አምስተኛ የሆነ መርሐግብር በአርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ መካከል ተከናውኗል፡፡ያለ አሰልጣኝ መሠረት ማኔ ዛሬ ወደ ሜዳ የገባው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ካደረገው እንቅስቃሴ ወረድ ብሎ ሜዳ ላይ የታየ ሲሆን በአንፃሩ አስገራሚ የሜዳ ላይ የጨዋታ ሲስተምን ይዘው የገቡት አርባምንጭ ከተማዎች በበኩላቸው ኳስን መሠረት ባደረገ እንቅስቃሴ በተጋጣሚያቸው ላይ መውሰድ የቻሉበት ነበር፡፡
ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ወደ ጎል ከመድረስ ያገዳቸው ነገር ባይኖርም 38ኛው ደቂቃ ላይ ወርቅነሽ መልሜላ ከርቀት ያስቆጠረችው ግብ በሁለተኛው ሳምንት አርፎ ለመጣው የአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ቡድን ሦስት ነጥብ በማስገኘት ጨዋታው 1-0 ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ግብ አስቆጣሪዋ ወርቅነሽ መልሜላ የቤቲካ የጨዋታ ሽልማትን አግኝታለች፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 ድሬዳዋ ከተማ
የመጨረሻ የስድስተኛ ሳምንት መርሐግብር በሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ፍፁም በሆነ የፈረሰኞቹ እንሴቶች ብልጫ የተጠናቀቀ ነበር፡፡ ገና 3ኛው ደቂቃ ላይ ዳግማዊት ሰለሞን ባደረገችው ያለቀለት ሙከራ ጥቃት መሰንዘራቸውን አሀዱ ብለው የጀመሩ ሲሆን በተደጋጋሚ በቅብብሎሽ ሂደት የድሬዳዋ ተጫዋቾችን ስህተት በደንብ በመጠቀም ብልጫን ማሳየት ችለዋል፡፡
ፈጣኗ የመስመር አጥቂ ታደለች አብርሃ ካደረገችው ብቸኛ ሙከራ ውጪ ይህ ነው የሚባል የግብ አጋጣሚን ለመፍጠር ያልታደሉት ድሬዳዋ ከተማዎች በተቃራኒው ጥቃቶች ሲሰነዘርባቸው ውሏል፡፡20ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ የድሬዳዋ የግብ ክልል ከራቀ ቦታ ላይ ሶፋኒት ተፈራ እጅግ አስገራሚ ጎል አስቆጥራ ጊዮርጊስን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡ ይህ ጎል ሲቆጠር የድሬደዋ ግብ ጠባቂ አበባየው ጣሰው በአጥቂዋ ዳግማዊት ሰለሞን ላይ አደገኛ ጥፋት ሰርታለች በመባሉ በአራተኛ ዳኛዋ ፀሀይነሽ አበበ ጥቆማ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዳለች፡፡
አጥቂዋ ዳግማዊት በጉልበቷ ላይ ጠንከር ያለ ጉዳትን በማስተናገዷ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የህክምና ባለሙያ ባለመኖሩ የቀይ መስቀል ዕርዳታ ከሚሰጡት ሙያተኞች በተሻለ በአሁኑ ሰዓት የሲዳማ ቡና የህክምና ባለሙያ ብሩክ ደበበ ወደ ሜዳ ዘሎ በመግባት የመጀመሪያ የህክምና አገልግሎት ለተጫዋቿ ከሰጠ በኋላ በአምቡላንስ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሆስፒታል በአምቡላንስ አምርታለች፡፡
በጎዶሎ ተጫዋች የቀሩትን ደቂቃዎች ለመጫወት የተገደዱት ድሬዳዋ ከተማዎች አሁንም ሲበለጡ ታይቷል፡፡የመጀመሪያው አርባአምስት ሊጠናቀቅ ጥቂት ሲቀር ከመስመር ተሻግሮ የመጣ ኳስን የድሬዳዋ ተከላካይ ዘቢብ ኃይለስላሴ ጨርፋው ሲያልፋት እየሩስ ወንድሙ ወደ ጎልነት በቀላሉ አስቆጥራው ወደ 2-0 ክለቧን አሻግራለች፡፡
ከዕረፍት መልስ አከታትለው ተጫዋቾችን ቀይረው ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ ሜዳ ቢገቡም አሁንም የቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ የሜዳ ላይ ብልጫ ከሙከራ ጋር ማየት የተቻለበት ነበር፡፡ ይሁን እና ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት 2ለ0 ተደምድሟል፡፡
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊሷ ሶፋኒት ተፈራ የቤቲካ የጨዋታ ተሸላሚ ሆናለች፡፡