“በእግርኳስ ምንም የማይቻል ነገር የለም” ጌታነህ ከበደ

የዋሊያዎቹ የፊት መስመር ተሰላፊ ከካፍ ኦንላይን ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል።

33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሊጀምር ቀናቶች ቀርተውታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ቀደም ብሎ ወደ ስፍራው በማምራት የመጨረሻ ዝግጅቱን እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህ ስብስብ ውስጥ ዋሊያዎቹ ከስምንት ዓመታት በፊት በአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ሲሳተፉ የቡድኑ አባል የነበረው እና የአሁኑ የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ ከካፍ ኦንላይን ጋር አጭር ቆይታ ነበረው።

ጌታነህ እንደቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች በውድድሩ ላይ እንዲኖረው ስለሚፈልገው ድርሻ አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት “እንደአጥቂ ሁል ጊዜም ጎል እንድናስቆጥር ይጠበቅብናል። በአፍሪካ ዋንጫ ላይ መጫወት ትልቅ ትርጉም አለው። እኔም ሀገሬን ወደ ቀጣይ ዙር ለማሸጋገር ግቦችን ለማስቆጠር እጅጉን እፈልጋለሁ።” ብሏል።

ኢትዮጵያ በመጪው እሁድ በሚጀመረው ትልቁ የአህጉሪቷ ውድድር ላይ በመጀመሪያው ምድብ ከካሜሩን ፣ ቡርኪናፋሶ እና ኬፕቬርድ ጋር እንደተደለደለች ይታወቃል። አምበሉ የምድብ ተፋላሚዎቹን አስመልክቶ ከካፍ ኦንላይን ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ “በእግርኳስ ምንም የማይቻል ነገር የለም።” ያለ ሲሆን ” ዋናው ማድረግ የሚገባን በአግባቡ መዘጋጀት ፣ ትኩረት ማድረግ እና እንደቡድን መጫወታችን ላይ ነው።” በማለት ሀሳቡን አጠቃሏል። የወልቂጤ ከተማው አጥቂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኮትዲቯርን በማጣሪያው መርታት መቻሉ አሁንም የትኛውንም ቡድን የማሸነፍ አቅም እንዳለው እንደሚያሳይም ዕምነቱን ገልጿል።

ጌታነህ ከበደ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን በሦስቱም የምድብ ተፋላሚዎች ኒጀር ፣ ማዳጋስካር እና ኮትዲቯር ላይ ማስቆጠር መቻሉ ይታወሳል።