​ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዳማ እና ሀዋሳ  ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ረፋድ ላይ ሲደረጉ አዳማ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማን 2ለ1 ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ከጨዋታ ብልጫ ጋር ጌዲኦ ዲላን 3ለ0 በመርታት ወሳኝ ነጥብ ይዘዋል፡፡

3፡00 ሲል የቦሌ ክፍለከተማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ መደረግ ጀምሯል፡፡ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት ጨዋታ በአንፃራዊነት ቦሌ ክፍለ ከተማዎች ኳስን በመቆጣጠር ረገድ በተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫ ወስደው ታይተዋል። በተለይ ቡድኑ በአንድ ሁለት ቅብብል መነሻቸውን ከመሀል እና ከመስመር ካጋሉ ቦታዎች በማድረግ ወደ ንግስት በቀለ እና ጤናዬ ለታሞ በማድላት ለመጫወት ሰሞክር ቢታይም አዳማ ከተማዎች በረጃጅም ኳስ እና በመጠኑም ቢሆን ከተሻጋሪ ኳስ ጎል ለማግኘት ሲታትሩ ተስተውሏል፡፡ ይህ ቢሆንም ግን በ8ተኛው ደቂቃ ከግራ የቦሌ የግብ ክልል የተገኘ የቅጣት ምት ሲሻማ ኤደን ሽፈራው በግንባር ገጭታ አዳማን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች፡፡ ግቧ ስትቆጠር ከመስመር አላለፈችም በሚል ተቃውሞ በዳኞች ላይ ቢቀርብም ፌዴራል ረዳት ዳኛ ፀደቀች አበራ ጎሉ መስመር ማለፉን በጥቆማዋ አረጋግጣ ጨዋታው በአዳማ መሪነት ሊቀጥል ችሏል፡፡


ፅዮን ፈየራ ካደረገችሁ ሙከራ ውጪ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ያልታደሉት አዳማዎች 39ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ተቆጥሮባቸዋል፡፡ አምበሏ ሰናይት ኢርኮ ከቀኝ የአዳማ የግብ ክልል ወደ ሳጥኑ በመንደርደር ላይ ላለችሁ ንግስት በቀለ አቀብላት ታዳጊዋ ተጫዋች ቦሌን 1ለ1 ማድረግ ስትችል ለራሷ ደግሞ በአመቱ አምስተኛ ጎሏን አስፅፋላች፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች የአዳማዋ ግብ ጠባቂ እምወድሽ ይርጋሸዋ ከፍ ያለ ንቃት ባይታይባት ኖሮ ተጨማሪ ግቦች ባስተናገዱ ነበር፡፡ ቦሌዎች የአዳማን የተከላካይ መስመር ቶሎ ቶሎ በመረበሽ ወደ ጎል መድረስ ቢችሉም ግብ ጠባቂዋ ፈጥና እየወጣች በተደጋጋሚ ዕድሎቹ እንዲመክኑ ስታደርግ ተስተውሏል፡፡


ከእረፍት መልስ ጨዋታው ልክ በመጀመሪያው አጋማሽ ስናስተውላቸው የነበሩ የጨዋታ እንቅስቃሴዎችን በድጋሚ በዚህኛው አጋማሽ መመልከት ብንችልም የቦሌ ክፍለ ከተማ የመከላከል መንገድ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ግን በአዲስ መልክ የተመለከትነው ጉዳይ ሆኗል፡፡ ነገር ግን ቡድኑ ኳስን ከማንሸራሸር ያገደው የሌለ ቢሆንም አዳማ ከተማዎች በፍጥነት ከመልሶ ማጥቃት መነሻ በሆኑ ረጃጅም ኳሶች ጥቃት ለመሰንዘር ጥረትን አድርገዋል፡፡ ልክ ሁለቱ ቡድኖቹ ወደ ሜዳ እንደተመለሱ በአንድ ሁለት ቅብብል ቦሌዎች በቶሎ የአዳማ ሳጥን ደርሰው በመጨረሻም ጤናዬ ለታሞ ግልፅ የማስቆጠር ዕድልን ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ አስቆጠረች ተብሎ ሲበበቅ በቀላሉ ልታመክነው ችላለች፡፡


በኳስ ቁጥጥሩ መበለጣቸውን የተረዱት አዳማ ከተማዎች በረጃጅም ኳስ ሁለቴ ቦሌ የግብ ክልል ደርሰው አንደኛውን ወደ ጎልነት ቀይረውታል፡፡ ሳምራዊት ሀይሉ ከቀኝ በኩል በቀጥታ ወደ ግብ መታ ማህሌት ሽፈራው ከያዘቸባት በኋላ ሁለተኛ ያገኙትን ዕድል በአግባቡ ተጠቅመውበታል፡፡ 54ተኛው ደቂቃ ላይ መሰሉ አበራ ከራሷ የግብ ክልል በረጅሙ ስታሻግር የቦሌ ተከላካዮች ጨርፈውት ባለበት ሰአት ሰርካዲስ ጉታ ፍጥነቷን ተጠቅማ በማፈትለክ ለአዳማ ሁለተኛው ጎል አስቆጥራለች። በቀሩት ደቂቃዎች ቦሌዎች አቻ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ጨዋታው 2ለ1 በሆነ የአዳማ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡


ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የቦሌዋ አጥቂ ንግስት በቀለ የቤቲካ የጨዋታ ኮከብ ሽልማትን አግኝታለች፡፡

5፡00 ሲል የአራተኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ እና ጌዲኦ ዲላ መካከል ተከናውኗል፡፡ ከእለቱ ዳኛ ሲሳያ ራያ የማስጀመሪያ ፊሽካ አንስቶ እስከ ፍፃሜው ድረስ በጨዋታ ረገድም ሆነ በርካታ ሙከራን በማድረጉ ሀዋሳ ከተማዎች ፍፁማዊ ብልጫን ሲያሳዩ የዋሉበት ቢሆንም እንዳገኙት ላቅ ያለ የግብ አጋጣሚ ኳስ እና መረብን ማገናኘት የቻሉት ግን ሦስት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ጨዋታው 9ኛው ደቂቃ ላይ እንደደረሰ ከማዕዘን ምት ረድኤት አስረሳኸኝ ስታሻማ የመሀል ተከላካዩዋ ቅድስት ዘለቀ በግንባር በመግጨት ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡አዲስ ንጉሴ 15ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ሞክራ በቀላሉ ፍሬወይኒ ገብሩ ከያዘችባት ሙከራ ውጪ ጌዲኦ ዲላዎች የሀዋሳ የግብ ክልል ለመድረስ አልታደሉም።


ሀዋሳ ከተማዎች መሀል ላይ ህይወት ረጉ እና ሲሳይ ገብረዋህድ በፈጠሩት አስደናቂ ስብጥር መነሻነት በአንድ ሁለት ቅብብሎሽ ከፊት ለተሰለፉት አጥቂዎች በተደጋጋሚ ማሻገር ቢችሉም ዝንጉነትን የተላበሱት የሀዋሳ አጥቂዎች ሲያመክኑን በተደጋጋሚ ተመልክተናል፡፡ በረድኤት ፣ ነፃነት ፣ ቱሪስት እና ህይወት አማካኝነት የግብ ዕድሎችን ፈጥረው መጠቀም ሳይችሉ የቀሩት የአሰልጣኝ መልካሙ ታፈረ ተጫዋቾች 41ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛው ጎል አግኝተዋል፡፡ ከመልስ ውርወራ ያገኘችሁን ኳስ ዙፋን ደፈርሳ በቀጥታ ለረድኤት አስረሳኸኝ አቀብላት የፊት አጥቂዋ ሁለቴ ገፋ በማድረግ ከመረብ አዋህዳዋለች፡፡ ከጎሉ መቆጠር አንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ ነፃነት መና ከህይወት ረጉ ያገኘችውን ኳስ ካለ ግብ ጠባቂ ከግቡ ቋሚ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝታ በሚያስቆጭ መልኩ ስታዋለች፡፡


በሁለተኛውም አጋማሽ የሀዋሳዎች ይበልጥ ጫና ፈጥሮ መጫወትን ያየንበት ሲሆን በርካታ አጋጣሚንም ከመጀመሪያው አጋማሽ በበለጠ አግኝተው ሳጥን እየደረሰ ሲያመክኑ የዋሉበት ነበር፡፡ በረድኤት ፣ ነፃነት ፣ ቱሪስት እና ተቀይራ በገባችሁ ቁምነገር ካሳ አማካኝነት እጅግ አደገኛ ሙከራዎችን በተደጋጋሚ እያገኙ መጠቀም አልቻሉም፡፡ 55ተኛው ደቂቃ ላይ ረድኤት አስረሳኸኝ በሚደንቅ ዕይታ ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረችሁ ነፃነት መና አቀብላት የጌዲኦ ዲላን ግብ ጠባቂ መኪያ ከድርን መውጣት ተመልክታ ሦስተኛውን የሀዋሳን ጎል ማስቆጠር ችላለች፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች በርካታ ተጨማሪ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ዕድሎችን ሀዋሳዎች ቢያገኙም ጨዋታው 3ለ0 በሆነ ውጤት ተደምድሟል፡፡


ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሀዋሳዋ አጥቂ ነፃነት መና የቤቲካ የጨዋታ ኮከብ ሽልማትን አግኝታለች፡፡