ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የአሪያት ኦዶንግ ብቸኛ ግብ አዲስ አበባ ከተማን አሸናፊ አድርጋለች

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት ሦስተኛ ጨዋታ መከላከያ እና አዲስ አበባ ከተማን አገናኝቶ የአሪያት ኦዶንግ ድንቅ አጨራረስ አዲስ አበባ ከተማን የ1-0 አሸናፊ አድርጓል፡፡

10፡00 ሰዓት ሲል የአራተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሦስተኛ ጨዋታ የመዲናይቱ ክለቦች የሆኑትን መከላከያ እና አዲስ አበባ ከተማን ያገናኘ ነበር፡፡ ተመሳሳይ ይዘት ያለውን ፉክክር ባየንበት የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ በተቀናጀ የጨዋታ ፍሰት ወደ ጎል በመድረስ የአሰልጣኝ የሺሐረግ ለገሰው አዲስ አበባ ከተማ በአመዛኙ የተሻለ ሆኖ መታየት ችሏል። በአንፃሩ መከላከያ በአጥቂዎቹ አማካኝነት ከተሻጋሪ ኳሶች ቀላል የማይባሉ ዕድሎችን ማግኘት ቢችልም ሴናፍ እና ረሂማ በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ በሆነ አቋቋም ላይ መገኘታቸው የኋላ ኋላ ቡድኑን ዋጋ ማስከፈሉ ግድ ሆኗል፡፡

24ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል መጫወት የጀመሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ትርሲት መገርሳ ፣ ቤተልሄም ሰማን እና በመጨረሻም አሪያት ኦዶንግ እግር የደረሰው ኳስ አጥቂዋ ሁለት ተጫዋቾች አልፋ ወደ ግብነት በመለወጥ ቡድኗን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡ ከጎሉ በኋላ ምላሽ ለመስጠት ከቅጣት ምት አጋጣሚን መከላከያዎች አግኝተው ሴናፍ ብትመታውም ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶባታል፡፡ በቀሩት የአጋማሹ ደቂቃዎች ኳስን ቡድኖቹ በፈለጉት የጨዋታ መንገድ ከመጫወት በዘለለ የጠራ አጋጣሚን መፍጠር ሳይችሉ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ፍፁም መረጋጋት የተሳናቸው መከላከያዎች የተጫዋች ለውጥ ካደረጉ በኋላ በተወሰነ ረገድ ሻል ብለው ታይተዋል፡፡በተለይ በግራ መስመር በኩል እፀገነት ግርማ ተቀይራ ከገባች በኋላ ረጃጅም ኳሶችን ኢላማውን በጠበቀ መልኩ ለአጥቂዎች በማድረስ ቢሳካላትም የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ወደ ጨዋታ እንዲመለሱ አላስቻላቸውም፡፡ 50ኛው ደቂቃ ላይ የተረጋጋ የአንድ ሁለት ቅብብል በማድረግ የመከላከያ የግብ ክልል አዲስ አበባ ከተማዎች ደርሰው ቤተልሄም ሰማን ከትርሲቲ መገርሳ ያለቀለትን ዕድል አግኝታ መጠቀም ሳትችል የቀረችበት እና 57ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማን ኳስ ቤተልሄም በድጋሚ አግኝታ ሁለተኛ ጎል የሚሆን አጋጣሚን ያመከነችበት ሌላኛው የሰማያዊ ለባሾቹ ሙከራ ነበረች፡፡

ጨዋታው ሊጠናቀቅ አስር ደቂቃዎች ሲቀሩ ኃይላቸውን በማጥቃት ላይ አመዝነው መጫወታቸውን የጀመሩት መከላከያዎች ተደጋጋሚ ሙከራን ቢያደርጉም የሚፈጥሩት የመጨረሻ የሳጥን ውስጥ ያልተጠበቁ ስህተቶች ዋጋ ሲያስከፍላቸው ተመልክተናል፡፡83ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ሴናፍ በቀጥታ ወደ ጎል መትታ ግብ ጠባቂዋ ቤተልሄም ዮሐንስ በአስደናቂ ሁኔታ ያወጣችባት ምናልባት መከላከያን አቻ ለማድረግ የቀረበች ነበረች፡፡ 87ኛው ደቂቃ ላይ ለአዲስ አበባ ግብ ያስቆጠረችው አሪያት ኦዶንግ ወደ ጎል እየሄደ ያለን ኳስ በእጅ በመመለሷ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ በቀይ ካርድ የተወገደች ሲሆን ጨዋታውም 1-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የአዲስ አበባዋ አምበል ትርሲት መገርሳ የጨዋታው ምርጥ ተብላ በቤቲካ አምርተዋል፡፡

ያጋሩ