​ዋልያው ተጨማሪ አንድ ተጫዋች በነገው ጨዋታ ላያገኝ ይችላል

ከሰዓታት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሽመልስ በቀለን በነገው ጨዋታ እንደማያገኝ ያስነበብን ሲሆን ተጨማሪ አንድ ተጫዋችም በጉዳት የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።

በጉጉት የሚጠበቀው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በነገው ዕለት በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ካሜሩን ሲጀመር በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ካሜሩን፣ ኬፕ ቨርድ እና ቡርኪና ፋሶ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በመክፈቻው ቀን ሁለተኛ ጨዋታ የኬፕ ቨርድ አቻውን ይገጥማል። በስብስቡ ውስጥ ከኮቪድ ጋር ተያይዞ ምንም አሉታዊ ዜና ባይሰማም መጠነኛ የጉዳት ጉዳዮች እየተነሱ ይገኛሉ።

በግብፁ ክለብ አል ጎውና የሚጫወተው ሽመልስ ከጡንቻ ጋር ተያይዞ ጉዳት ማስተናገዱን እና ለነገው ጨዋታ መድረሱ አጠራጣሪ መሆኑን ቀድመን ያስነበብን ሲሆን አሁን በደረሰን መረጃ ደግሞ የአዳማ ከተማው አጥቂ ዳዋ ሁቴሳም መጠነኛ የቁርጭምጭሚት ጉዳት አስተናግዷል። የዳዋ ጉዳት ያን ያህል ለክፉ የሚሰጥ ባይሆንም እንደ ሽመልስ የእርሱም መሰለፍ አጠራጣሪ መሆኑ ተመላክቷል።

ያጋሩ