👉”በቡድናችን ያለውን ቀለም ለማሳየት ሰዓቱ አሁን ነው” ውበቱ አባተ
👉”የነገውን ጨዋታም በጥሩ ሁኔታ እየተጠባበቅን ነው” ጌታነህ ከበደ
👉”ያሉንን ባለ-ተሰጥኦ ወጣት ተጫዋቾች ለማሳየት እንሞክራለን” ውበቱ አባተ
👉”የተሻለ ነገር አሳይተን ያልታሰቡ (Surprise) ቡድኖች ከሚሆኑት ውስጥ ለመካተት እንሞክራለን” ውበቱ አባተ
በኮቪድ-19 ምክንያት አንድ ዓመት የተገፋው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ በነገው ዕለት በካሜሩን ይጀመራል። በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ካሜሩን፣ ኬፕ ቨርድ እና ቡርኪና ፋሶ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ወደ ስፍራው አቅንቶ ልምምዱን ሲሰራ የከረመ ሲሆን ከነገው ጨዋታ በፊት የመጨረሻ ልምምዱንም ከሰዓታት በኋላ ያከናውናል። ከጨዋታው በፊት ደግሞ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና አምበሉ ጌታነህ ከበደ ለ21 ደቂቃዎች በካሜሩን ከተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ጋር የቅድመ ጨዋታ ቆይታ አድርገዋል። በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከ9:30 ጀምሮ በተከናወነው መግለጫ ላይም በቅድሚያ የቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ ተከታዩን ብለዋል።
“ካሜሩን የደረስነው ቀድመን ነው። የእኛ ቡድን ካሜሩን የገባ የመጀመሪያው ቡድንም ነው። እንደምታቁት በዚህ ውድድር ከስምንት ዓመታት በኋላ ነው የተመለስነው። አሁን ደግሞ በሁሉም ነገር ተዘጋጅተን ነው የቀረብነው። በምድቡም ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ ተዘጋጅተናል። በተቻለን አቅምም ተፋልመን የራሳችንን ቀለም በሜዳ ላይ ለማሳየት እንጥራለን።” ብለዋል። በመቀጠል ደግሞ አምበሉ ጌታነህ ከበደ ይህንን ብሏል።
“ለጨዋታው ተዘጋጅተናል። አጋጣሚ ከ8 ዓመታት በፊት ወደ አፍሪካ ዋንጫው ስናልፍ እኔም ተሳትፌያለው። አሁን ለሁለተኛ ጊዜ ነው በአፍሪካ ዋንጫው የምሳተፈው። ካሜሩን ቀደም ብለን ነው የገባነው። የነገውን ጨዋታም በጥሩ ሁኔታ እየተጠባበቅን ነው።” የሚል አጭር ሀሳቡን አጋርቷል። በተከታይነት ከተለያየ የአህጉራችን ክፍል የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ጥያቄዎችን እያቀረቡ አሠልጣኙ እና አምበሉ ምላሽ መስጠት ጀምረዋል።
በአፍሪካ ዋንጫው ቪ ኤ አር ሊተገበር ስለመሆኑ?
“ለእኛ ለመጀመሪያ ጊዜያችን ነው። አብዛኞቹ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በሀገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ናቸው። በሊጋችን ደግሞ ይህ መሳሪያ የለም። ይህ አዲስ ተሞክሮ ነው። ግን ደግሞ በውድድሩ የሚሳተፍ የትኛውም ቡድን በሜዳ ላይ ባሳየው ብቃት ልክ ነው ውጤት ማግኘት ያለበት። ስለዚህ ይህ ጥሩ ነው። ባለፈውም ስለ ቫር የወሰድነው ትምህርት አለ። ስለዚህ ምንም ችግር የለውም ለእኛ።” ውበቱ አባተ
ብሔራዊ ቡድኑ ትንሽ ግምት ስለመሰጠቱ?
“ሁሉም ሰው እንደሚለው ኢትዮጵያ ትንሽ ግምት ነው የተሰጣት። የካፍ እና ፊፋ ደረጃ ይህንን ሊያመላክት ይችላል። ግን ደረጃው ያለንን ነገር በትክክል ይገልፃል ብዬ አላምንም። በምድባችን ያሉት ሦስቱም ብሔራዊ ቡድኖች ጠንካሮች ናቸው። ጥሩ ተጫዋቾችም አሏቸው። እኛ ደግሞ ያለንን ቀለም ለማሳየት ተዘጋጅተናል። በቡድናችን ጥሩ ጥሩ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች ስላሉ በስብስቡ እምነት አለኝ። በቡድናችን ያለውንም ቀለም ለማሳየት ሰዓቱ አሁን ነው። ማንም ሊያስበን አይችልም። ግን በማጣሪያው ያሳየነውን ነገር ታውቃላችሁ። ቡድኑ ጥሩ ይጫወታል። ግን ደግሞ ሁሉም ነገሮች ሜዳ ላይ ምላሽ ያገኛሉ።” ውበቱ አባተ
ከካሜሩን ጋር ስለመደልደላቸው?
“ሁሉም ነገር ጥሩም መጥፎም ነገር አለው። ካሜሩን ጠንካራ ቡድን ነው። ደግሞም በራሳቸው ሜዳ ነው የሚጫወቱት። ደጋፊዎችን ጨምሮ የሚያገኙት ብዙ ጥቅም አለ። ይህ ሊጠቅማቸው ይችላል። ግን በሌላ በኩል ከታየ ጫና ሊያመጣባቸው ይችላል። እኛ ከዚህ ጫና ነፃ ነን።
“ጨዋታዎቹ ቀላል ናቸው እያልኩ አደለም። ውድድሩ ትልቅ ውድድር ነው። አህጉራዊ ውድድር ነው። ቀላል ጨዋታም አይኖርም። ያልኩት ማንንም ቡድን አግዝፈን አናይም ነው። እናከብራቸዋለን። ግን የተለየ ምስል አንሰጣቸውም።” ውበቱ አባተ
በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ስላደረገለቸው ከባባድ ጨዋታዎች?
“ከጋና ጋር ከመጫወታችን በፊት ከአይቮሪ ኮስት ጋር ተጫውተን ነበር። በጨዋታዎቹ ጥሩ ነገር ነበር ያሳየነው። ከጋናም ጋር የነበረው ውጤት ጨዋታውን አይገልፀውም። ጥሩ ተንቀሳቅሰን ነበር። ጨዋታዎቹ ከአፍሪካ ዋንጫ በፊት በመሆናቸው አቋማችንን አይተንበታል።” ጌታነህ ከበደ
ከጉዳት እና ኮቪድ ጋር በተያያዘ?
“ካሜሩን ስንደርስ የተወሰኑ ተጫዋቾች ከኮቪድ ጋር በተያያዘ አብረውን አልነበሩም። አምስት ተጫዋቾች ለ7 ቀናት አብረውን አልሰሩም። ከ7 ቀናት በኋላ ግን ተቀላቅለውን ልምምድ እየሰሩ ነው። አሁን ላይ ሁሉም የቡድኑ አባላት ከኮቪድ-19 ነፃ ናቸው። ይህ በጣም መልካም ነገር ነው። ከጉዳት ጋር ተያይዞ ሽመልስ በቀለ እና ዳዋ ሁቴሳ የተወሰነ ጉዳት አጋጥሟቸዋል። ሽመልስ የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት ነው። ዳዋ ደግሞ የቁርጭምጭሚት ጉዳት ነው ያጋጠመው። ሁለቱም ነገ የመግባታቸው ጉዳይ ላይ ጥርጣሬ አለን። ከእነሱ ውጪ ግን ሁሉም ሰላም ናቸው።” ውበቱ አባተ
ከቡድኑ ምን ይጠበቅ?
“ከዚህ ቀደም አንድ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን አሸንፈናል። 11 ጊዜም ተሳትፈናል። ግን ደግሞ ለስምንት ዓመታት ከውድድሩ ርቀን ነበር። አሁን ውድድሩ ላይ ነን። የነበረን እቅድ አፍሪካ ዋንጫው ላይ መሳተፍ የሚል ነበር። ከአይቮሪኮስት እና ኒጀር ጋር ተጫውተን ይሄንን አሳክተናል። ከዛ ደግሞ በውድድሩ ተሳትፎ ከመምጣት ባለፈ ለአህጉራችን እና ለዓለም ያለንን ለማሳየት አስበናል። በተለይ ደግሞ ያሉንን ባለ-ተሰጥኦ ወጣት ተጫዋቾች ለማሳየት እንሞክራለን። በሌላ በኩል ሁላችሁም እንደምታቁት ምድቡ ጠንካራ ምድብ ነው። በውድድሩ ልምድ ያላቸው ሀገራትም አሉ። ግን የተሻለ ነገር አሳይተን ያልታሰቡ ቡድኖች ከሚሆኑት ውስጥ ለመካተት እንሞክራለን። ምድቡንም አልፈን ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ሀሳብ አለን። ለዚህ ደግሞ ሁሉም የሚጀምረው ከነገው ጨዋታ ጀምሮ ነው።” ውበቱ አባተ
ስለ ነገው ጨዋታ?
“የነገው ጨዋታ የመጀመሪያ ጨዋታ ነው። ሁለታችንም ቡድኖች እኩል ዕድል አለን። እኛም ከጨዋታው የተሻለ ነገር ለማምጣት እንሞክራለን። ኬፕ ቨርድ ጠንካራ ቡድን ነው። ግን ልዩነት የሚፈጥር ነገር እንደምንሰራ በራስ መተማመኑ አለን። በምድባችን ስለሚገኙት ሦስቱም ቡድኖች መረጃ አለኝ። ማንም ጠንካራ እንደሆኑ ያውቃል። ግን ደግሞ ይህ ለራሳቸው ነው። እኛ እናከብራቸዋለን። ውድድር ላይ ግን ሁሉም እኩል ነው። እነሱን አግዝፈን የምናይበት አንዳች ምክንያት የለም። ይህ እግርኳስ ነው።” ውበቱ አባተ
ካሜሩን ቀድመው ስለመግባታቸው?
“እቅዳችን የነበረው ሳውዲ አረቢያ ለመሄድ እና እዛ ለመዘጋጀት ነበር። ከጉዞ እቀባ ጋር ተያይዞ ግን እቅዳችንን ለውጠን ወደ ካሜሩን መተናል። ይህ ለእኛ ጥሩ ነው። ትልቅ ጥቅምም አለው። እኛ እዚህ ልንመጣ ስንል የአፍሪካ ዋንጫ ላይካሄድ ይችላል የሚል ሀሳብ ይነሳ ነበር። እኛ ካሜሩን እንደደረስን ግን ውድድሩ እንደሚካሄድ ለሁሉም ማረጋገጫ ሰጠን። እዚህ ከደረስን በኋላ ብዙ አትርፈናል። ከሱዳን ጋርም የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አከናውነናል። ከዚህ ውጪ የአየር ሁኔታውንም ለመልመድ እጅግ ጠቅሞናል።” ውበቱ አባተ