​ሪፖርት | ዋልያው ለሰማያዊው ሻርክ እጅ ሰጥቷል

በምድብ አንድ የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ ኬፕ ቨርድ ኢትዮጵያን 1-0 አሸንፏለች።

የአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ተጫዋቾች ኳስ መስርተው ለመጫወት ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም በኬፕቨርዴዎች ጫና መነሻነት የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ግብ ክልል አካባቢ ነበር። የግብ ማግባት ሙከራ ሳያስመለክት የቀጠለው ጨዋታው ገና 10 ደቂቃ ሳይሞላው ያልተጠበቀ ክስተት አስተናግዷል። በዚህም አስቻለው ታመነ በግንባሩ አቀብላለው ብሎ የተሳሳተውን ኳስ ያሬድ ባየህ የኬፕ ቨርዲው አጥቂ ሁሊዮ ታቫሬስ ሊጠቀምበት ሲጥር ጥፋት ሰርቶበት ጨዋታው ቆሟል። የዕለቱ ዳኛ ሄልደር ማርቲንስ ዲ ካርቫልሆ በቅድሚያ ለያሬድ ቢጫ ካርድ ቢሰጡትም በረዳቶቻቸው ጥቆማ በቪ ኤ አር ቅፅበቱን አይተው ተጫዋቹን በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥተውታል።

ገና በጊዜ መጥፎ ነገር ያጋጠማቸው ዋልያዎች በመከላከሉ ረገድ መሳሳት እንዳይታይባቸው መስዑድ መሐመድን አስወጥተው ምኞት ደበበን አስገብተው ጨዋታውን ማከናወን ቀጥለዋል። ቀይ ካርዱን ተከትሎ ተቀይሮ የገባው ምኞት ደበበ ደግሞ በ27ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረን ኳስ ለማፅዳት ሲጥር ተሳስቶ ከራሱ መረብ ጋር ሊያዋህደው ነበር። ነገርግን የግብ ዘቡ ተክለማርያም ሻንቆ በጥሩ ቅልጥፍና አውጥቶታል። የቁጥር ብልጫውን ለመጠቀም የጣሩት ኬፕ ቨርዶች ጨዋታው ሲጀመር የተወሰደባቸውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በማግኘት ለመንቀሳቀስ ጥረዋል። በ34ኛው ደቂቃም ዳግም በቀኝ መስመር በመሄድ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ የፈጠሩ ቢሆንም ዕድሉን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችም በጊዜ በተፈጠረው ክስተት ሳይደናገጡ ጌታነህ እና አቡበከርን ያማከለ የማጥቃት አጨዋወት ለመተግበር ሲጥሩ ታይቷል። በተለይ የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት ከመሐል የተላከን ኳስ የመሐል ተከላካዩ ሮቤርቶ ካርሎስ በደረቱ ለግብ ጠባቂው አቀብላለው ሲል አቡበከር ደርሶ ኳስ እና መረብን ሊያገናኝ ነበር። ነገርግን ግብ ጠባቂው ማርሲዮ ዳሮሳ ፈጥኖ በመውጣት ኳሱን አምክኖታል። ክፍለ ጊዜው አልቆ በተጨመረው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ያመሩት ኬፕ ቨርዶች ፍሬያማ ሆነው ተመልሰዋል። በዚህም ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ጋሪ ሮድሪጌዝ በሩቁ ቋሚ በመጠበቅ ያገኘውን ኳስ በቀኝ እግሩ ለሁሊዮ ታቫሬስ አቀብሎት ታቫሬስ በግንባሩ ግብ አስቆጥሯል። አጋማሹም በኬፕ ቨርድ መሪነት ተገባዷል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ዋልያዎቹ ወደ ጨዋታው ለመመለስ በጌታነህ አማካኝነት ጥቃት ለመሰንዘር ሞክረው ተመልሰዋል። ሰማያዊ ሻርኮቹ ደግሞ የግብ ልዩነቱን ለማስፋት ሲሞክሩ ነበር። በተለይ በመስመር ላይ ፈጣን ሽግግሮችን በማድረግ ጫና ለማሳደር ጥረዋል። 62ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ደግሞ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ሁለት የአጥቂ አማካዮችን ቀይረው አስገብተው ከጨዋታው አዎንታዊ ነገር ይዞ ለመውጣት አስበዋል። በዚህም ጌታነህ እና አማኑኤልን በፍሬው እና ፍፁም ለውጠው በላይኛው የሜዳ ክፍል የተሻለ የኳስ ፍሰት እንዲኖር ጥረዋል።

70ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ መሪዎቹ በግራ የሳጥኑ ክፍል ኬኒ ሳንቶስ አግኝቶ በሞለረው ኳስ ሁለተኛ ግብ ሊያገኙ ነበር። ነገርግን ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ሲያመክን የነበረው ተክለማርያም አውጥቶበታል። ከ8 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ይሄው ተጫዋች ከሳጥን ውጪ ሌላ ኳስ አክርሮ ወደ ግብ መትቶ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል። በቀሪ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች የሰላ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሳይፈጥሩ ጨዋታው በኬፕ ቨርድ አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ከኢትዮጵያ እና ኬፕ ቨርድ ጨዋታ በፊት በዚሁ ምድብ የሚገኙት ካሜሩን እና ቡርኪና ፋሶ ተፋልመው ካሜሩን አሸንፋለች። የምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታዎችን ተከትሎም ምድቡን አዘጋጇ ሀገር ካሜሩን ስትመራ ኬፕ ቨርድ ብዙ ባገባ በሚለው ተበልጣ ሁለተኛ ሆናለች። ቡርኪና ፋሶ እና ኢትዮጵያ ደግሞ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታውን የፊታችን ሀሙስ ምሽት አንድ ሰዓት ከአዘጋጇ ሀገር ካሜሩን ጋር የሚያከናውን ይሆናል። ኬፕ ቨርድ ደግሞ ከቡርኪና ፋሶ ጋር ትጫወታለች።

 

ያጋሩ