የአፍሪካ ዋንጫ ልዩ ዘገባ ከካሜሩን | የሽመልስ በቀለ ወቅታዊ ሁኔታ

በጉዳት ምክንያት የመጀመሪያውን ጨዋታ ያላደረገው የሽመልስ በቀለ ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ የተጠናቀረ ዘገባ።

የብሔራዊ ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች የሆነው ሽመልስ በቀለ ባጋጠመው የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት ምክንያት ከትናቱ የኬፕ ቬርድ ጨዋታ ውጪ መሆኑ ይታወቃል። በዛሬው ረፋድ የብሔራዊ ቡድኑ ልምምድ ወቅት ግን ሽመልስ በሦስት ምዕራፍ የተከፈለ እንቅስቃሴ ሲያከናውን ታዝበናል።

በመጀመርያው ምዕራፍ ለብቻው ተነጥሎ ወደ አስራ አምስት ደቂቃ አካባቢ የቆየ ሜዳውን በመዞር የመሮጥ ሥራ ሰርቷል። የተወሰነ ዕረፍት ካደረገ በኋላ በወጌሻ ሂርባ ፋኖ አማካኝነት የሰውነቱን ጡንቻ እንዲላቀቅ ተደርጓል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የብሔራዊ ቡድኑ የፊትነስ ባለሙያ ከሆኑት ዶ/ር ዘሩ በቀለ ጋር አብሮ በመሆን የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ወደ ሃያ ደቂቃ ያህል ሲሰራ ተመልክተናል። በተጨማሪም በመጀመርያው ምዕራፍ በተመለከትነው ዓይነት ዶ/ር ዘሩ የሽመልስን የእግር ጡንቻዎች የማላቀቅ ሥራዎችን አከናውነውለታል።

በሦስተኛው እና በመጨረሻው ምዕራፍ እንቅስቃሴ በትናትናው ጨዋታ ተቀይረው የገቡት እና ያልተጫወቱት ተጫዋቾች ለሁለት ተከፍለው በግማሽ ሜዳ ጠንካራ ጨዋታ ባደረጉበት ወቅት በአንደኛው ቡድን ውስጥ በመካተት ለአርባ ደቂቃ ያህል ሲጫወት ተመልክተነዋል።

በአጠቃላይ ሽመልስ በቀጣይ ሐሙስ ከካሜሩን ጋር ለሚኖረው ጨዋታ እንዲደርስ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የታዘብን ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ ከሥፍራው ካገኘችው መረጃ አኳያ ከጨዋታው በፊት የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ከሜሩንን የመግጠም ዕድሉ ሰፊ ነው።

ግብጠባቂው ፋሲል ገ/ሚካኤል እና ዳዋ ሁቴሳ ያሉበትን ሁኔታ አስመልክቶ ከቆይታ በኋላ መረጃዎችን ይዘን የምንመለስ ይሆናል።