የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለወሳኙ ጨዋታ ዝግጅቱን ጀምሯል

በአሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከፊቱ ላለበት የታንዛኒያ ጨዋታ ልምምዱን ዛሬ ጀምሯል።

የወቅቱ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ባለ ክብሮቹ በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የአህጉሩን የማጣሪያ ጨዋታዎች እያደረጉ ይገኛል። ቡድኑም በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዙር ማጣሪያም ከሩዋንዳ እና ቦትስዋና ጋር ጨዋታውን አድርጎ ወደ አራተኛ ዙር ፍልሚያ ማለፉ ይታወሳል። በአራተኛ ዙርም ከታንዛኒያ አቻው ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታውን ያከናውናል።

ለዚህ ወሳኝ ፍልሚያ ከሁለት ቀናት በፊት ጥሪ ያቀረቡት የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤልም ስብስባቸውን በትናንትናው ዕለት በተሟላ ሁኔታ ካገኙ በኋላ ዛሬ ረፋድ የመጀመሪያ ልምምድ አሰርተዋል። በካፍ የልህቀት ማዕከል ማረፊያውን ያደረገው ስብስቡም በ35 ቀበሌ ሜዳ የመጀመሪያ ልምምዱስ ሲያከናውን ሁሉም ተጫዋቾች መገኘታቸውን አስተውለናል። ለ60 ደቂቃዎች በቆየው ልምምድም ተጫዋቾቹ ቀለል ያሉ ሥራዎችን እንዲሰሩ ተደርጓል።

በስብስቡ እንደ አዲስ ጥረ የቀረበላቸው ማክዳ ዓሊ፣ ትዕግስት ኃይሌ፣ አይናለም አደራ፣ ቅድስት ቴቃ፣ ንግስት በቀለ፣ ሰናይት ሼጎ እና ንጋት ጌታቸውም ከአጋሮቻቸው ጋር ሲሰሩ አስተውለናል። ብሔራዊ ቡድኑ ለአንድ ሳምንት ልምምዱን ቀን በቀን እያከናወነ ከዘለቀ በኋላ ጥር 13 ለሚደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ወደ ዳሬ ሰላም የሚያቀና ይሆናል።

ያጋሩ