የመክፈቻ ጨዋታውን ትናንት ያከናወነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዛሬው ዕለት ልምምዱን ሰርቷል።
በምድብ ሀ የተደለደለችው ኢትዮጵያ ትናንትና የምድቧን የመጀመርያ ጨዋታዋን ከኬቨርድ ጋር በማድረግ በጠባብ ውጤት መሸነፏ ይታወሳል። ቡድኑ ከትናትናው ጨዋታ መልስ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከስድስት ሰዓት ጀምሮ ለአንድ ሰዓት የቆየ ልምምድ ሰርቷል።
ለሁለት በተከፈለው የልምምድ መርሐ ግብር በአንኛው ወገን በትናትናው ጨዋታ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ የተጫወቱ እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ውስጥ ተቀይረው የወጡ ተጫዋቾች ተነጥለው ቀለል ያሉ የማገገም ልምምዶችን ከተለያዩ አዝናኝ እንደ ፍፁም ቅጣት ምት ያሉ ልምምዶች ጋር ለአርባ ደቂቃዎች ያህል ሰርተው እንዲያርፉ ተደርጓል። ከዚህ ስብስብ ውስጥ ታፋው ላይ መጠነኛ መቁሰል ያጋጠመው ሱራፌል ዳኛቸው ህክምና ሲደረግለት ቆይቷል።
በሁለተኛው ምድብ የሚገኙት በትናትናው ጨዋታ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ያልተጠቀሙባቸው ተጫዋቾችን ጨምሮ ተቀይረው በመግባት የተጫወቱት ተጫዋቾች አንድ ላይ በመሆን አስቀድሞ ቀለል ያለ ኳስን መሠረት ያደረገ ልምምድ ካከናወኑ በኋላ በግማሽ ሜዳ ለሁለት ተከፍለው እርስ በእርስ ግጥሚያ አድርገዋል።
የቡድኑ መንፈስ እና ለቀጣዩ ጨዋታ ያለው ተነሳሽነት መልካም መሆኑን በታዘብንበት በዛሬው ልምምድ ከሽመልስ በቀለ ፣ ዳዋ ሆቴሳ እና ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ውጪ ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ አውቀናል። ከአንድ ስዓት በላይ ቆየው የዛሬው ልምምድ በህብረት በመሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ መዝሙርን በመዘመር ፍፃሜውን አግኝቷል።
ነገም በተመሳሳይ ልምምዶችን የሚሰሩት ዋልያዎቹ በቀጣይ ሐሙስ የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታን ከካሜሩን ጋር የሚያደርጉ ይሆናል።