የአፍሪካ ዋንጫ ልዩ ዘገባ ከካሜሩን | ሽመልስ በቀለ ለሐሙሱ ጨዋታ ይደርስ ይሆን ?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለሐሙሱ ጨዋታ ልምምዱን የቀጠለ ሲሆን ሽመልስ በቀለ የዛሬውን ልምምድ አቋርጦ ሲወጣ ተመልክተናል።

በሽመልስ በቀለ የጉዳት ሁኔታን አስመልክቶ በትናንትናው ዘገባችን በሦስት ምዕራፍ የተከፈሉ ልምምዶችን በተሳካ ሁኔታ እንዳጠናቀቀ እና የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ለካሜሩን ጨዋታ እንዲደርስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልፀን ነበር። በዛሬው የልምምድ መርሐግብሩን በጥሩ ሁኔታ እያከናወነ ይገኝ የነበረው ሽመልስ ለሁለት ተክፍሎ በተደረገው ጨዋታ ላይ የጡንቻ መሳሳብ ጉዳቱ አገርሽቶበት በሀዘን ስሜት ልምምዱን አቋርጦ ወጥቷል።

ከክስተቱ በኋላ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ሲያፅናኑት የታዩ ሲሆን የቡድን አጋሮቹ ጀማል ጣሰው እና ጌታነህ ከበደም ሲያረጋጉት ተመልክተናል። ከከልምምዱ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከአሰልጣኝ አባላቶቻቸው ጋር በመሆን የህክምና ቡድኑን በመጥራት ሽመልስ በተገኘበት በጉዳቱ ዙርያ ውይይት አድርገዋል። የውይይቱ መጨረሻ ምን አንደሆነ ለጊዜው መረጃ ባናገኝም ለቀጣይ ጨዋታ ሽመልስ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ አድርጎታል።

ያጋሩ