ድሬዳዋ ከተማ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሾሟል

አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስን ያገደው የምስራቁ ክለብ ጊዜያዊ አሰልጣኝ በዛሬው ዕለት መሾሙ ታውቋል፡፡

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተሳተፉ ካሉ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ድሬዳዋ ከተማ ከሰሞኑ ዋና አሰልጣኙ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስን ማገዱን በዘገባችን ጠቁመን ነበር፡፡ በዘንድሮው ውድድር የዘጠኝ ሳምንታት የሀዋሳ ጨዋታዎች ላይ በአሰልጣኙ መሪነት ሁለት ጨዋታ አሸንፈው አራቱን ተሸንፈው በቀሩት አቻ ወጥተው በ11 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ 13ኛ ላይ በመቀመጣቸው የክለቡ የቦርድ አመራሮች ፕሪምየር ሊጉ በተቋረጠበት ወቅት ባደረጉት አስቸኳይ ውይይት አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ያስመዘገቡት ውጤት ዝቅተኛ ነው በማለት እስከ ዓመቱ መጨረሻ ውል ያላቸውን አሰልጣኝ አግዷል፡፡

በዛሬው ዕለት ደግሞ የክለቡ የቦርድ አመራሮች ባደረጉት ውይይት ለቀጣዮቹ ስድስት ጨዋታዎች ማለትም በድሬዳዋ ስታዲየም ለሚደረጉት መርሀግብሮች የሚሆን አሰልጣኝ መርጧል፡፡ በዚሁም መሠረት የድሬዳዋ ከተማ ክለብን በቴክኒክ ዳይሬክተርነት እያገለገሉ የነበሩት ፉዓድ የሱፍን የክለቡ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በ80ዎቹ እግር ኳስን ለድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ እና ምድር ባቡር የተጫወቱት እና በአሰልጣኝነቱ ሀረር ከነማን በ90ዎቹ መጀመሪያ በዋና እና ረዳት አሰልጣኝነት የሰሩ ሲሆን ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማሳደግም ይታወቃሉ፡፡

ከሀረር ከነማ በመቀጠል በሀረር ቢራ ረዳት አሰልጣኝነት ቦታ ላይ ሆነው ያገለገሉት አሰልጣኙ ለቀጣዮቹ ስድስት ጨዋታዎች ውጤትን መሠረት አድርጎ በሚቀጥል ውል የክለቡ ጊዜያዊ አሰልጣኝ በመሆን ዛሬ ተመርጠዋል፡፡