የአፍሪካ ዋንጫ ልዩ ዘገባ ከካሜሩን | የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዛሬ ልምምድ ውሎ

ከኬፕቨርድ ጨዋታ መልስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዛሬው ዕለት የሁለተኛ ቀን ልምምዱን አድርጓል።

ትናንት ልምምድ ባደረገበት ተመሳሳይ ሰዓት ዛሬም ረፋድ ላይ ለሁለት ሰዓት የቆየ ልምምድ የሰራው ብሔራዊ ቡድኑ የተለያዩ ታክቲካዊ ሥራዎችን ከውኗል። ሁለት ሁለት ሆነው ኳስ በመቀባበል የጀመሩት የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ከተወሰነ ደቂቃ በኋላ የማላቀቅ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርገው ወደ ሌላኛው ልምምዳቸው አምርተዋል። ከ30 ደቂቃ ባልበለጠው በቀጣዩ ልምምዳቸው ኳሱን እንደ ቡድን የመቀባበል ዘዴን መሰረት በማድረግ እንዴት ወደፊት መሄድ እንዳለባቸው በድግግሞሽ ሲለማመዱ አይተናል።

ይህንን እንደጨረሱ በቡድን ሆነው ከሳጥን ውጪ ወደ ጎል የመሞከር ሥራ ሰርተዋል። በማስቀጠል የመጨረሻ ልምምዳቸው የነበረው እና ምን አልባት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከኬቨርድ ጨዋታ የመጀመሪያ አስራ አንድ ላይ ለውጥ ሊያደርጉ እንዲሚችሉ የሚጠቁም ልምምድ አድርገዋል።

ለሁለት ተከፍለው የግማሽ ሜዳ ታክቲካዊ ልምምድ ሲያደርጉም ኳሱን ተቆጣጥሮ በመጫወት ወደፊት አስከፍቶ ወደ ጎል የመቀየር ልምምድ ሰርተዋል። በአንደኛው ቡድን ውስጥ በግብ ጠባቂነት ተክለማርያም ሻንቆ ከእርሱ ፊት አስራት ቱንጆ ፣ ምኞት ደበበ ፣ አስቻለው ታመነ እና ረመዳን የሱፍ አማካይ ቦታ ላይ አማኑኤል ዮሐንስ ፣ መስዑድ መሐመድ እና ሱራፌል ዳኛቸው ከፊት ደግሞ ዳዋ ሁቴሳ ፣ አቡበከር ናስር እና ፍሬው ሰለሞንን በመጠቀም ሰርተዋል።

ከሽመልስ በቀለ እና ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ውጪ ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኙ ሲሆን ከነገው የመጨረሻ ልምምዳቸው አስቀድሞ በዛሬው ዕለት የኮቪድ ምርመራ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታ በቀጣይ ሐሙስ ምሽት አንድ ሰዓት ከካሜሩን ጋር እንደሚያደርግ ይጠበቃል።