በሁለቱም ፆታዎች ሀገርን ወክለው የሚሳተፉ ትምህርት ቤቶችን ለመለየት የሚረዳው እና የፓን አፍሪካኒዝምን ፅንሰ ሀሳብ ለማስፋፋት የተለመው ውድድር በሀገራችን ዛሬ ተጀምሯል።
የዓለም እግርኳስ የበላይ አካል በሆነው ፊፋ እና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ሀሳብ አመንጪነት ከወራት በፊት ወደ ስራ እንዲገባበት አቅጣጫ የተቀመጠው የፓን አፍሪካ የትምህርት ቤቶች ውድድር በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በይፋ እንደተጀመረ ይታወቃል። በሁለቱም ፆታዎች እድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሚገኙ ታዳጊ ተጫዋቾችን የሚያሳትፈው ውድድርም በአህጉር አቀፍ ደረጃ በቀጣይ ወር የመግባቢያ ሰነድ ቀድሞ በተፈረመበት ኮንጎ እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞለታል። በዚህ ውድድር ከሚሳተፉ ስድስት ቡድኖች መካከል ዕድሉን ያገኘችው ሀገራችን ኢትዮጵያም ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት ባለፈ በውድድሩ የሚሳተፉትን የወንድ እና የሴት የትምህርት ቤት ቡድኖች ለመለየት ዛሬ ውድድር ማድረግ ጀምራለች።
የኢፌዲሪ የባህል እና ስፖርት ሚኒስተር፣ የኢፌዲሪ የትምህርት ሚኒስተር እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በጋራ ያዘጋጁት ውድድር ዛሬ ረፋድ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በደማቅ ሁኔታ ሲጀመር በመክፈቻ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እና የትምህርት ሚኒስቴር አጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ ዶ/ር ፈንታ አበበን ጨምሮ ከተለያዩ የስፖርት ተቋማት የተገኙ የስፖርት አመራሮች ተገኝተዋል።
ዊልዋል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ሱማሌ)፣ አቦከር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጎሮ ቡቲጂ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ድሬዳዋ)፣ ዱና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ደቡብ)፣ አዋሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ኦሮሚያ) እና እንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት (አዲስ አበባ) በወንዶች ፆታ የሚሳተፉ ሲሆን በሴቶች ደግሞ ማርያም ሰፈር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ድሬዳዋ)፣ ዲላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ደቡብ)፣ አዋሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ኦሮሚያ) እና እንጦጦ አምባ (አዲስ አበባ) የሚሳተፉ ይሆናል።
ስምንት ተጫዋቾች 70 በ50 በሆነ ሜዳ ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ረፋድ 5 ሰዓት ላይ ሲጀምር ዲላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማርያም ሰፈር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን 9ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል። ነገ እና ከነገ በስትያ ጨዋታዎች ቀጥለውም ሀሙስ የውድድሩ ማብቂያ ይሆናል።