👉”ነገ እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ እንታገላለን” ውበቱ አባተ
👉”በእግር ኳስ ሁሌም ትልቁ ጨዋታ በቀጣይ የምታደርገው ነው” መስዑድ መሐመድ
👉”ሁሉም ሰው ወታደር ሊሆን አይችልም። እኛ ደግሞ በሙያችን ወታደር ነን” ውበቱ አባተ
👉”ጨዋታውን ብንሸነፍ ሁሉንም ነገር አናጣም። ማሸነፍ ወይም መሸነፍ የዓለም ፍፃሜ አይደለም…” ውበቱ አባተ
👉”ለሀገራችን ህዝብም ሆነ ለመንግስታችን ምላሽ ማቅረብ አለብን” መስዑድ መሐመድ
በ33ኛው የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ ውድድር ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነገው ዕለት ከውድድሩ አዘጋጅ ካሜሩን ጋር የምድብ ሁለተኛ ጨዋታውን በኦሊምቤ ስታዲየም ያከናውናል። ከጨዋታው አስቀድሞም የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና የአማካኝ መስመር ተጫዋቹ መስዑድ መሐመድ ከደቂቃዎች በፊት የቅድመ ጨዋታ አስተያየት ለካሜሩን የብዙሃን መገናኛ አባላት ሰጥተዋል። በቅድሚያም አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በተነሱለት ጥያቄዎች መሰረት ተከታዩን ምላሽ ሰጥቷል።
ስለ ኬፕ ቨርዱ ጨዋታ?
ከኬፕ ቨርድ ጋር ያደረግነው ጨዋታ ከሌሎቹ ጨዋታዎች ይለያል። ቀይ ካርድ በየትኛውም ጨዋታ ይከሰታል። ግን በጊዜ ተጫዋችን ማጣት ከእቅድህ እንድትወጣ ያደርግካል። የነገው የካሜሩን ጨዋታ ሌላ ጨዋታ ነው። በነገው ጨዋታ የሚኖረን የጨዋታ አቀራረብ ከኬፕ ቨርድ ጋር ከአስረኛው ደቂቃ በኋላ እንደተጫወትነው አይደለም። በጨዋታውም ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በምትጫወተው መንገድ ለመጫወት እንሞክራለን።
በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው ብዙ ግቦችን አስቆጥረናል። በኬፕ ቨርድ ጨዋታ ግን የግብ ዕድሎችንም አልፈጠርንም። ይህ የሆነው ደግሞ ጨዋታውን በመቆጣጠር ሰዓት መያዝ ስለፈለግን ነበር። ይህንን ብናስብም ግን የተዋጣልን አልነበረም። በጨዋታው የነበረው ጥሩ ነገር ሌሎች ግቦችን አለማስተናዳችን ነው። ይህ ለተጫዋቾቹ ትልቅ ጥቅም ይሰጣል። የግብ ልዩነት በውድድሩ ስለሚያስፈልግም ይህንን ተጫዋቾቼ አድርገዋል። እንደተባለው የግብ ማግባት ሙከራዎችን ያልሞከርነው እና የግብ ዕድሎችን ያልፈጠርነው በጎዶሎ ተጫዋች ስለተጫወትን ነው። ወደ ሜዳ ስንገባ ለመከላከል አስበን አልነበረም። ሁሉም ነገሮች የተቀየሩት ቀይ ካርዱ ከተከሰተ ነበር።
ስለካሜሩን ቡድን እና ከዚህ ቀደም ስለተገናኙበት ጨዋታ?
ከካሜሩን ጋር ከዚህ ቀደም ተጫውተናል። ግን በቻን ውድድር ነው የተጫወትነው። እኛ በቻንም ሆነ በዋናው የአፍሪካ ዋንጫ በተመሳሳይ መንገድ ነው የምንቀርበው። የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን ግን በቻን ካጫወታቸው ተጫዋቾች ውጪ ሌሎች ከሀገር ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾች አሉት። እንደምትመለከቱት በአፍሪካ ዋንጫው ካሜሩን ያላት ስብስብ ውስጥ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከሀገር ውጪ የሚጫወቱ ናቸው። ግን እኛ ጋር ይህ የለም። በቻንም ሆነ በአፍሪካ ዋንጫው የምንጠቀማቸው ተጫዋቾች ሀገር ውስጥ የሚጫወቱ ናቸው። የነገው ጨዋታ እንደ ቻኑ ጨዋታ ቀላል አይሆንም። አሁን እኛ የምንጫወትበት ከባቢም ከባለፈው ጋር አንድ አይደለም። አሁን በሜዳቸው ነው የምንጫወተው። ቡድኑም ትልቅ እቅድ እና የሆነ ነገር ለሀገሩ ለማምጣት የሚጥር ነው። ይህ ትልቅ ለውጥ ነው። ምንም ቢሆን ምንም ግን እኛ ስለ ቀደመው ነገር አናስብም። ከቡርኪና ፋሶም ጋር ሲጫወቱም አይተናቸዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን መስርታ አንድ ጊዜ ብቻ ዋንጫ ስለማንሳቷ?
ልክ ነው። ለአፍሪካ ዋንጫ አዲስ አደለንም። በውድድሩ 11 ጊዜ ተሳትፈናል። ግን አንድ ጊዜ ብቻ ነው ዋንጫ ያነሳነው። ይህ ሊያስገርም ይችላል። አደለም ዋንጫውን ማሸነፍ በውድድሩ አንድ ጨዋታን ካሸነፍን እንኳን ቆይተናል። ስለዚህ ይህንን ለማስተካከል በርትተን መስራት አለብን። ይህንንም ለማድረግ መንገድ ጀምረናል። ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ መድረኩ ተመልሰናል። ከዚህም በኋላ በውድድሩ የምንሳተፍበትን ጊዜ መደጋገም ያስፈልጋል። ከዛ በኋላ ደግሞ ስለ ዋንጫው ማውራት እንጀምራለን። ትልቅ ሀገር እንደመሆናችን ግን ልክ ነው ዋንጫ ያስፈልገናል።
የካፍ መስራች እንደመሆኗ በዓለም አቀፍ መድረክ አልታየችም። ኢትዮጵያ በእግርኳሱ ከወደቀችበት እየተነሳች ነው ብለህ ታምናለህ?
የአፍሪካ ዋንጫ ጀማሪ ከሆኑ ሀገራት መካከል ነበርን። የውድድሩ ቻምፒዮን እና የፍፃሜ ተፋላሚም ነበርን። ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ተመልሰን ነበር። አሁን ደግሞ ከስምንት ዓመታት በኋላ ተመልሰናል። በቀጣይ በየሁለት እና አራት ዓመቱ እንደምንሳተፍ ተስፋ አድርጋለሁ። የእኛ እግርኳስ ማደግ ጀምሯል፣ ብዙ እምቅ አቅም ያላቸው ወጣቶችም አሉን። ያም ሆኖ ያለንን ለማሳየት እና የተሻለ ለማድረግ የገንዘብ አቅም ያስፈልጋል።
ስለ መጀመሪያው ጨዋታ ውጤት?
ከኬፕ ቨርድ ጋር ከ80 ደቂቃ በላይ በጎዶሎ ተጫዋች ነው የተጫወትነው። ይህ ጨዋታውን ለመጨረስ ለተጫዋቾቹ ከባድ ነው። እስካሁን ያሉትን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ውጤት ካያችሁም 1-0 እና 2-1 እንዲሁም 0-0 የተመዘገቡባቸው ናቸው። የእኛም ቡድን አንድ ለምንም ነው የተረታው። ግቡም ደግሞ የተቆጠረብን በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ነው። ምናልባት ከትኩረት ማነስም ሊሆን ይችላል ጎሉ የገባብን። በጨዋታው ጠንካራ ነበርን። ግን እንደ ከዚህ ቀደሙ ጠንካራ አልነበርንም። ይህ የሆነውም ጎዶሎ ስለነበርን ነው። በሜዳ ላይ 11 አልነበርንም። ባለፉት አምስት እና ስድስት ጨዋታዎች በወጥነት የተሻልን ነበርን። ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባቡዌ ከመሳሰሉት ጋር የተሻልን ነበርን። በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ጨዋታውን በመቆጣጠር ረገድ። የተሻሉ ቁጥሮች ነበሩን።
በኢትዮጵያ ያለው ውጥረት ለዝግጅት አስቸጋሪ ሆኖባቸው ነበር?
አዎ እንዳልከው ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች ነበሩ። ይህ እግርኳሱን ብቻ ሳይሆን ሁሉም ነገር ላይ ተፅእኖ ፈጥሮብን ነበር። እውነት ለመናገር እንዲህ ባለ ትልልቅ ውድድር ላይ ከ24 ሀገራት መካከል ሰንደቅ አላማችንን ስመለከት ከፍተኛ ኩራት ተሰምቶኛል። እዚህ ቀድመን ነበር የመጣነው። ምክንያቱም ሳውዲ መሄድ አልቻልንም ነበር። በዚህ ትልቅ ውድድር ላይ ለመሳተፍ በመምጣታችን ፣ ለሀገራችን እና በተከሰተው ግጭት ተፅእኖ ውስጥ ለገቡ ሁሉ ወክለን ስለተገኘንም ደስተኞች ነን።
በሀገራችን እየተፈጠረ ያለውን ነገር አናስብም እያልኩኝ አደለም። ግን አሁን እኛ ትኩረታችን ኳሱ ላይ ነው። የትኛውም ተጫዋች ሜዳ ገብቶ ኳስ ሲነካ ከሜዳ ውጪ ያሉትን ነገሮች መርሳት አለበት። ሁሉም ሰው ወታደር ሊሆን አይችልም። እኛ ደግሞ በሙያችን ወታደር ነን። እኛ ሀገራችንን የወከልነው በእግርኳሱ ነው። ስራችንም እግርኳስ ነው። ስለዚህ ትኩረታችንን እዚህ ላይ እናደርጋለን። ግን ደግሞ በሀገራችን የሚፈጠረው የትኛውም ነገር እንደ ሰው ልባችንን ይነካዋል። በቅርቡም በሀገራችን ሰላም ሆና ወደ ጠንካራነቷ እንደምትመለስ ተስፋ አለኝ።
ስለ ነገው የካሜሩን ጨዋታ?
በነገው ጨዋታ ጠንካራ ቡድን እንደምንገጥም ነው የምንጠብቀው። በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት ነው የሚጫወቱት። እኛም እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ እንታገላለን። ምናልባት ቀላል ስህተቶችን ከተሳሳትን እንደባለፈው ጨዋታ ዋጋ ልንከፍል እንችላለን። ግን ላረጋግጥ የምፈልገው ነገር በሜዳ ላይ የቻልነውን ያህል ለማሳየት እንጥራለን። ጨዋታውን ብንሸነፍ ሁሉንም ነገር አናጣም። ማሸነፍ ወይም መሸነፍ የዓለም ፍፃሜ አይደለም። በቀጣይም ሌሎች ውድድሮች ይኖራሉ። ቀጣይ የአፍሪካ ዋንጫ ይኖራል። ይህን ማለት ግን የነገውን ጨዋታ እንሸነፋለን ከውድድርም እንወጣለን ማለት አይደለም። ከቡርኪና ፋሶ ጋር የምናገደርገው የመጨረሻ ጨዋታ ላይ የመጨረሻ እድላችንን ተጠቅመን ለማለፍ እንጫወታለን።
ከአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር መግለጫ ለመስጠት የተሰየመው አማካዩ መስዑድ መሐመድም ጥያቄዎች ቀርበውለት ምላሽ ሰጥቷል።
በማጣርያው ላይ የነበረው ብቃት እዚህ ያልታየበት ምክንያት?
ለብዙዎቻችን ይህ ትልቅ ውድድር የመጀመርያችን ነው። በርካታ ተጫዋቾችም ወጣቶች ናቸው። በእግር ኳስ ሁሌም ትልቁ ጨዋታ በቀጣይ የምታደርገው ነው። የኬፕ ቨርዱ ጨዋታው አልፏል። አሁን ከካሜሩን ጋር ለሚደረገው ጨዋታ ተዘጋጅተናል። በአእምሮው ለመዘጋጀት ተነጋግረናል። በነገው ጨዋታ እንታገላለን።
ሀገራቸው ስለሰጣቸው ሀላፊነት እና የፀጥታ ሁኔታ?
እንደ ማንኛውም ሰው ሀገራችን ሁሌም ሰላም እንዲሆን እንፈልጋለን። መንግስታችንም እዚህ መተን በደንብ እንድንዘጋጅ በሚገባ ረድቶናል። ስለዚህ ለሀገራችን ህዝብም ሆነ ለመንግስታችን ምላሽ ማቅረብ አለብን። ለእኛ ትልቅ ክብር ሰጥተውናል። እኛም የሀገራችንን ባንዲራ ከፍ በማድረግ ጥሩ ምላሽ ለመስጠት እናስባለን።