የአፍሪካ ዋንጫ ልዩ ዘገባ | ዋልያዎቹ ከነገው ጨዋታ አስቀድሞ የመጨረሻ ልምምድ አከናውነዋል

የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታ ነገ ከካሜሩን ጋር ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምሽት ላይ የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል።

ለአንድ ሰዓት በቆየው በዛሬው ልምምድ ቀለል ያሉ እና ከትናንትናው መርሐ ግብር ጋር ተመሳሳይ የሆኑ እንደቡድን የማጥቃት ስራዎች ሰርተዋል። ለሁለት ተክፍሎ በተደረገው የእርስ በእርስ ጨዋታ በአንደኛው ቡድን በኩል ለነገው ጨዋታ ፍንጭ በሚሰጥ መልኩ በግብጠባቂ ተክለማርያም ሻንቆ ፤ በመከላከሉ ሱሌይማን ሀሚድ፣ ምኞት ደበበ፣ አስቻለው ታመነ፣ ረመዳን የሱፍ በመሐል ክፍሉ አማኑኤል ዮሐንስ፣ መስዑድ መሐመድ እና ሱራፌል ዳኛቸው እንዲሁም በማጥቃቱ ረገድ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ፣ አቡበከር ናስር እና ዳዋ ሆቴሳ በመሆን ተጫውተዋል።

ከዛሬው ልምምድ በኋላ ሽመልስ በቀለ እና ግብጠባቂው ፋሲል ገ/ሚካኤል ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆናቸው ተረጋግጧል። በተጨማሪም በነገው ጨዋታ ምናልባትም ጌታነህ ከበደ በተጠባባቂ ወንበር ሊቀመጥ እንደሚችል እና በምትኩ መስዑድ መሐመድ ቡድኑን እየመራ ሊገባ እንደሚችል ይጠበቃል።

ብሔራዊ ቡድናችን ዛሬ ልምምዱን ሲያከናውን የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራን ጨምሮ የሥራ አሰፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣ የፌዴሬሽኑ የፅህፈት ቤት ሠራተኞች እንዲሁም የካፍ ቴክኒክ ጥናት ቡድን አባል በመሆን በስፍራው የሚገኙት ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ እና የዋልያዎቹ ደጋፊዎች በቦታው በመገኘት ተመልክተዋል።

ያጋሩ