በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎው ሁለተኛ የምድብ ጨዋታውን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በካሜሩን የ4-1 ሽንፈት አስተናግዷል።
ዋልያዎቹ ከመጀመሪያው ጨዋታ ቀይ ካርድ የተመለከተው ያሬድ ባየህ እና ጌታነህ ከበደን በምኞት ደበበ እና ዳዋ ሆቴሳ በመተካት ለካሜሩኑ ጨዋታ ቀርበዋል።
የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በመውሰድ ጨዋታውን የጀመሩት ዋሊያዎቹ ጥሩ ፉክክር ያደረጉበትን የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፈው ነበር። ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ብዙ ደቂቃ ሳይወስድባቸውም 4ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ የደረሱበትን አጋጣሚ ግብ አድርገውታል። አማኑኤል ገብረሚካኤል ከመስመር መሬት ለመሬት ወደ ሳጥን ያደረሰውን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ ከተከላካዮች አምልጦ በመግባት ግብ አድርጎታል። ሆኖም የኢትዮጵያዊያኑ መሪነት ለአራት ደቂቃዎች ብቻ የዘለቀ ነበር። 8ኛው ደቂቃ ላይ አምበሉ አቡበከር ቪንሰንት ከርቀት ያደረገውን ሙከራ ተክለማሪያም ሻንቆ ከመለሰበት በኋላ ከቀኝ በኩል ፋይ ኮሊንስ ያሻማውን ነፃ የነበረው ቶኮ ኢኬምቢ በግንባር በመግጨት ካሜሩንን አቻ አድርጓል።
የጨዋታው ፍጥነት ዝግ ባለባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች ቶሎ ናሁ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በየፊናቸው ቀላል ያሉ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቢስተዋልም ሁለቱም ቡድኖች እንደልብ ክፍተት ማግኘት አልቻሉም። ተጋጣሚያቸው ኳስ ሲይዝ ጠንቀቅ ብለው በራሳቸው ሜዳ ይቆዩ የነበሩት ዋሊያዎቹ ግን ቀጣዩን አደገኛ ዕድል ፈጥረዋል። 24ኛው ደቂቃ ላይ ከሱለይማን ሀሚድ በተነሳ ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከቀኝ መስመር በመነሳት ሳጥን ውስጥ ደርሶ ቢሞክርም ግብ ጠባቂው አንድሬ ኦናና መልሶበታል። ዳዋ የተመለሰውን ኳስ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረትም አልተሳካም።
ጨዋታው ሰላሳኛውን ደቂቃ ሲሻገር አመዛኙን የኳስ ቁጥጥር በእጃቸው ያደረጉት ካሜሩኖች ወደ ቀኝ ያመዘነ ጥቃታቸው እየበረታ ሄዷል። በእነዚህ ደቂቃዎች በሁለት አጋጣሚዎች የአስቻለው ታመነ የመጨረሻ ውሳኔዎች ካሜሮናዊያኑን ከአደገኛ ሙከራ አግዷል። ይሁን እና 39ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጣሪው ቶኮ ኢካምቢ ከማዕዘን የመጣን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በግቡ ብረት ተመልሶበታል። ይህንን ተከትሎ ዋሊያዎቹ በቁጥር ብልጫ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ዕድል አግኝተው ሳጥን ውስጥ ቢደርሱም ወደ ሙከራነት መቀየር አልቻሉም። ሆኖም በአጋማሹ ማብቂያ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን ውጪ ያደረገው አደገኛ ሙከራ ግብ እንዳይሆን የአንድሬ ኦናናን ብቃት የጠየቀ ነበር።
ከዕረፍት መልስ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የቢጫ ካርድ የተመለከተው ሱራፌል ዳኛቸውን በፍሬው ሰለሞን በመተካት ወደ ሜዳ ተመልሰዋል። ሆኖ በኢትዮጵያዊያኑ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የጀመረው አጋማሽ ጥሩ እንደተንቀሳቀሱበት የመጀመሪያው 45 አልሆነላቸውም። የበላይነታቸውን ለማሳየት ነገሮች የቀለሉላቸው ካሜሩኖች የባየርን ሙኒኩ ቾዎፕ ሞቲንግ 48ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ ወደ ሳጥን ባደረሰው ኳስ ለግብ ቢቃረቡም ተክለማሪያም ኳሱ የደረሰው የፊት አጥቂው ቪንሰንት አቡበከር ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት በሸርተቴ አውጥቶበታል። ሆኖም በዚሁ የኢትዮጵያ የግራ መስመር ሰብረው መግባት የቀጠሉት ካሜሩኖች በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ሁለት ግቦችን በቪንሰንት አቡበከር አማካይነት አስቆጥረዋል። አጥቂው 53ኛው ደቂቃ ላይ ኮሊንስ ፋይ ያሻማለትን በግንባር 55ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በዛው በቀኝ መስመር አጥብቦ ከገባው ሞዉምቲ ንጋማሉ የደረሰውን በቀላል አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።
በቀጣይ ደቂቃዎችም ዋሊያዎቹ መረጋጋት ተስኗቸው በተጋጣሚያቸው ሙሉ ብልጫ ተወስዶባቸው ቆይተዋል። ጨዋታው 60ኛውን ደቂቃ ሲሻገር በመጠኑ ወደ ራሳቸው ተመልሰው ወደ ካሜሩን የግብ ክልል መቅረብ ቢጀምሩም 67ኛው ደቂቃ ላይ ታኮ ኢካምቢ ከመሀል የተሰነጠቀለትን ኳስ በግራ በኩል በመግባት ተከላካዮችን አታሎ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ግብ አስቆጥሯል።
አህመድ ረሺድ ፣ በዛብህ መለዮ እና ሽመክት ጉግሳን ለውጠው ያስገቡት ዋሊያዎቹ በተመሳሳይ በርካታ ለውጦችን ካደረገው ተጋጣሚያቸው አንፃር ቀስ በቀስ ከኳስ ጋር የተረጋጋ ጊዜን ማሳለፍ ሲጀምሩ የማይበገሩት አንበሶች ጫናም ቀለል ብሏል። ጨዋታው 80ኛውን ደቂቃ ሲሻገር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የኳስ ቁጥጥር ወደ ተጋጣሚው ሳጥን ሲቀረብ ካሜሩኖችም በመልሶ ማጥቃት አደጋ ሲፈጥሩ ታይተዋል። ከሁሉም በላይ 87ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ጌታነህ ከበደ የካሜሩኖችን ኳስ የመጀመር ሂደት አቋርጦ ወደ ሳጥኑ ያደረሰው እና አበበከር ያልተጠቀመበትን ኳስ በዛብህ መለዮ ለማስቆጠር ቢቃረብም በሚያስቆጭ ሁኔታ ሙከራው ወደ ላይ ተነስቷል። ካሜሩኖችም በግቡ ቋሚ በተመለሰው የፋዬ ኮሊንስ የሳጥን ውጪ ሙከራ ምላሽ ሰጥተዋል። ይህ ሙከራ የጨዋታው መጨረሻ ሆኖ ጨዋታው በአዘጋጆቹ 4-1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።