ሀገር አቀፍ የፓን አፍሪካ የትምህርት ቤቶች ውድድር ዛሬ ሲጠናቀቅ በሁለቱም ፆታዎች ኢትዮጵያን ወክለው በአህጉራዊ መድረክ የሚሳተፉ ቡድኖችም ተለይተዋል።
የኢፌዲሪ የባህል እና ስፖርት ሚኒስተር፣ የኢፌዲሪ የትምህርት ሚኒስተር እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በጋራ ያዘጋጁት ይህ ሀገር አቀፍ ውድድር ከትናንት በስትያ በመዲናችን አዲስ አበባ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደተጀመረ ይታወቃል። በውድድሩ ዊልዋል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ሱማሌ)፣ አቦከር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጎሮ ቡቲጂ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ድሬዳዋ)፣ ዱና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ደቡብ)፣ አዋሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ኦሮሚያ) እና እንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት (አዲስ አበባ) በወንዶች ፆታ ማርያም ሰፈር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ድሬዳዋ)፣ ዲላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ደቡብ)፣ አዋሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ኦሮሚያ) እና እንጦጦ አምባ (አዲስ አበባ) ደግሞ በሴቶች ፆታ ዛሬን ጨምሮ ያለፉትን ሦስት ቀናት የተፋለሙ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በሁለቱም ፆታዎች ለፍፃሜ የደረሱት ቡድኖች የውድድሩን የመጨረሻ ጨዋታዎች አከናውነዋል።
ረፋድ ላይ በነበረው የመዝጊያ መርሐ-ግብር ቀድሞ የተከናወነው (የሴቶች) የዲላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የአዋሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጨዋታ ሙሉ 60 ደቂቃው አንድ አቻ ከተጠናቀቀ በኋላ በተሰጠው የመለያ ምት ከደቡብ ክልል የመጣው የዲላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 5ለ3 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ቀጥሎ በተከናወነው የወንዶች ጨዋታ ደግሞ አዋሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ዱና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገናኝተዋል። በዚህ ጨዋታም አዋሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ኦሮሚያ) ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር 5ለዐ በሆነ ውጤት አሸንፏል። ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ በታዘበችው መሰረትም ውድድሩ ከ16 ዓመት በታች ተጫዋቾችን እንደሚያካትት ቢነገርም አንዳንድ ተጫዋቾች ላይ አጠራጣሪ ነገሮች እንዳሉ አስተውላለች።
ውጤቶቹን ተከትሎም የዲላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና አዋሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ኢትዮጵያን ወክለው በኮንጎ ኬንሻሳ በሚካሄደው ውድድር ላይ መሳተፋቸውን አረጋግጠዋል። ከዚህ ውጪ በወንዶች ሳልዓዲን ጀማል ከዱና ትምህርት ቤት ኮከብ ተጫዋች፣ ተሰማ ሞት ከአዋሮ ትምህርት ቤት 8 ጎሎችን በማስቆጠር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሲሆን በተመሳሳይ ከአዋሮ ዳዊት ብሩክ ኮከብ ግብ ጠባቂ በመሆን ተመርጠዋል፡፡ በሴቶች ደግሞ አፀደ አቡ ከአዋሮ ትምህርት ቤት ኮከብ ተጫዋች ሆና ስትመረጥ ትንሳኤ ፀጋዬ ኮከብ ግብ ጠባቂ እንዲሁም ምትኬ ብርሃኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ከዲላ ትምህርት ቤት ተመርጠዋል።
የዋንጫ አሸናፊዎቹም ግዙፉ የትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ አሳምሮ በሰራው መድረክ ላይ ሽልማቶቻቸውን ከክብር እንግዶቹ ተረክበዋል። የአፍሪካ የትምህርት ቤቶች ውድድርም ከአንድ ወር በኋላ በኮንጎ የሚከናወን ይሆናል።