አራት ኢትዮጵያዊያን ሴት ዳኞች ካምፓላ ላይ የሚደረግ የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ጨዋታን ይመራሉ፡፡
ኮስታሪካ በ2022 ለምታስተናግደው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ለማድረግ በአፍሪካ የሚገኙ ሀገራት በማጣሪያው እየተካፈሉ የሚገኙ ሲሆን በቀጣዩ ሳምንት የአምስተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች በስምንት ሀገራት መካከል ይደረጋል። ደቡብ አፍሪካን በደርሶ መልስ የረታችው ዩጋንዳ እና በተመሳሳይ ዛምቢያን በማሸነፍ ወደዚህኛው ዙር የቀረበችው ጋናን የሚያገናኘውን ጨዋታም አራት ኢትዮጵያዊያን ሴት ዳኞች በዳኝነት ይመሩታል፡፡
ጥር 12 የሚደረገውን ይህን ጨዋታ በ2022 ፊፋ ካሳወቃቸው ዳኞች መካከል በዋና ዳኝነት ሊዲያ ታፈሰ በረዳት ዳኝነት እንደ ሊዲያ ሁሉ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ወይንሸት አበራ እና ብርቱካን ማሞ ሲመሩ በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ ፀሀይነሽ አበበ በካፍ ጥሪ የደረሳቸው ዳኞች ሆነዋል፡፡
የደርሶ መልስ ጨዋታዎች የሚደረጉበት ይህ ዙር ወሳኝ ጨዋታዎች በተመሳሳይ በሳምንቱ የሚደረጉ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ለመሸጋገር ታንዛኒያን ከሜዳዋ ውጪ ስትገጥሞ የዩጋንዳ እና ጋናን ጨዋታ ጨምሮ ሞሮኮ ከ ሴኔጋል፣ ካሜሩን ከ ናይጄሪያ በማጣሪያው የሚፋለሙ ይሆናል፡፡