በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው አዳማ ከተማ በድሬዳዋ ከተማ ለሚከናወነው ውድድር ከቀናት በፊት ዝግጅቱን ሲጀምር አምስት ተጫዋቾች ግን ልምምድ መስራት አልጀመሩም።
በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው አዳማ ከተማ በ9 ሳምንታት የሊጉ ጉዞ በ12 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ ይታወሳል። ሊጉ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲቋረጥ ለእረፍት ተጫዋቾቹን በትኖ የነበረው ክለቡም ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ለቀጣይ የሊጉ ጨዋታዎች ተጫዋቾቹን ጠርቶ ነበር። ክለቡ ያቀረበውን ጥሪ ሁሉም ተጫዋቾች (በብሔራዊ ቡድን ግዳጅ ላይ ከሚገኙት ውጪ) አክብረው ቢመጡም አምስት ተጫዋቾች ግን ልምምድ መስራት አለመጀመራቸውም ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
በመዲናችን አዲስ አበባ ሳሬም ሆቴል ማረፊያውን አድርጎ ሱሉልታ ከሰኞ ጀምሮ ልምምድ መስራት የጀመረው ስብስብ ውስጥም ሚሊዮን ሰለሞን፣ ጀሚል ያዕቆብ፣ አብዲሳ ጀማል፣ ቶማስ ስምረቱ እና ሴኩምባ ካማራ ቃል የተገባላቸው የማትጊያ ክፍያ በቀኑ እንዳልደረሳቸው በማንሳት ሆቴል ቢገቡም ከአጋሮቻቸው ጋር ያለፉትን አራት ቀናት ልምምድ አልሰሩም። በአሁኑ ሰዓትም ቡድኑ የዛሬ የልምምድ መርሐ-ግብሩን ሲያከናውን ተጫዋቾቹ አለመኖራቸውም አውቀናል።
በአዳማ ከተማ ክለብ ውስጥ ሊጉ የሦስት ሳምንታት ጨዋታዎችን አከናውኖ ለ20 ቀናት ሲቋረጥ አምስቱን ጨምሮ ሌሎች ተጫዋቾችም ከክፍያ ጋር ተያይዞ ባቀረቡት ጥያቄ ልምምድ አቁመው እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱም ከክለቡ አመራቶች እና የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ጋር በተደረገ ንግግር ተጫዋቾቹ ወደ ልምምድ መመለሳቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
ጉዳዩን በተመለከተ ከክለቡ አመራሮች ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለአሁን ባይሳካም የሚኖሩ አዳዲስ ነገሮችን እየተከታተልን የምናቀርብ ይሆናል።