የአፍሪካ ዋንጫ ልዩ ዘገባ ከካሜሩን| የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዛሬ ልምምድ ውሎ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከትናንቱ የካሜሩን ሽንፈት ማግስት ዛሬ ረፋድ ላይ ልምምዱን አከናውኗል።

ወደ ዋናው ልምምድ ከመግባታቸው በፊት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ረመዳን የሱፍ እና አስቻለው ታመነን በመለየት ውይይት ያደረጉ ሲሆን ወደ ዋናው ልምምድ ከመግባታቸው አስቀድሞ የማሟሟቅ እንቅስቃሴ አድርገዋል።

በመሐል ባልገባ የቀጠለው ሁለተኛው ምዕራፍ ልምምድ እንደተጠናቀቀ በትናንትናው ጨዋታ ሙሉ ዘጠና ደቂቃ የተጫወቱትን በማሳረፍ የቀሩት በግማሽ ሜዳ ለሁለት ተከፍለው እንዲጫወቱ ተደርጓል። በማስከተል የፍጥነት ስራ ከሰሩ ከአንድ ሰዓት ተኩል ቆይታ በኃላ ልምምዳቸው ተጠናቋል።

ነገ በቀጣይ ጨዋታቸውን ወደሚያደርጉበት ባፎሳ ከተማ በአውሮፕላን ጉዞ የሚያደርጉ ሲሆን ለቀናት ዝግጅታቸውን በዚሁ ከተማ በማድረግ የሚቆዩ ይሆናል።

ከጉዳት ጋር በተያያዘ ግብጠባቂው ፋሲል ገ/ሚካኤል እና አማካዩ ሽመልስ በቀለ ለቀጣዩ ጨዋታ የማይደርሱ መሆኑ ሲታወቅ መጠነኛ የጉልበት ጉዳት ያጋጠመው አቡበከር ናስር ለቡርኪናፋሶው ጨዋታ እንደሚደርስ ይጠበቃል።

ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ እድሏ ያልተሟጠጠው ኢትዮጵያ ሰኞ ምሽት ከቡርኪና ፋሶ ጋር በምታደርገው የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ላይ በሚመዘገበው ውጤት እታ ፈንታዋ የሚወሰን ይሆናል።