ቡርኪና ፋሶ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የሚጫወተው ወሳኝ ተጫዋቿን ጨምሮ ሦስት ተጫዋቾችን ከኮቪድ መልስ በነገው ጨዋታ ታገኛለች።
ሰባት ቀናት ያስቆጠረው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከነገ ጀምሮ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንደሚጀምር ይታወቃል። በዚህ ውድድር ተሳታፊ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከቡርኪና ፋሶ አቻው ጋር በሚያደርገው ፍልሚያ ነገ ምሽት 01:00 ላይ ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ያለውን ያልተሟጠጠ ዕድል የሚሞከር ይሆናል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በጨዋታው የተሻለ ዕድል ይዞ የሚገባው ተጋጣሚው የቡርኪና ፋሶ ብሔራዊ ቡድን በጨዋታው ወሳኝ ተጫዋቾቹን ከኮቪድ-19 መልስ እንደሚያገኝ ተመላክቷል። በዚህም መሰረት ለእንግሊዙ አስተን ቪላ እየተጫወተ የሚገኘው በርትራንድ ትራኦሬ ፣ በግብፅ ሊግ የሚጫወተው ሰይዶ ሲማፓዎሬ እና ሶማይላ ኦውታራ ለነገው የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ከኮቪድ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል።
በሌላ በኩል ግብ ጠባቂው ሄርቪ ኮፊ የኮቪድ ምርመራውን ባለማለፉ ለጨዋታው አይደርስም። ሆኖም አሰልጣኝ ካሙ ማሎ ተጨማሪ ሦስት ግብ ጠባቂዎችን በስብስባቸው በመያዛቸው ሁኔታው የተለየ ስጋት የማይፈጥርባቸው መሆኑ ይታመናል።