የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድቡን ሦስተኛ ጨዋታ ነገ ከማድረጉ አስቀድሞ የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል።
ከአስራ አምስት ቀን ባላይ ቆይታ ካደረገባት ሞቃታማዋ ከተማ ያውንዴ በመልቀቅ በትናንትናው ዕለት በአውሮፕላን ጉዞ ቀዝቃዛዋ መንደር ባንጉ የገባው ብሔራዊ ቡድኑ ታጊዶ ጋርደን ሪዞርት መቀመጫውን አድርጎ ትናንት እና ዛሬ ልምምዱን ሰርቷል። ነገ ምሽት ጨዋታውን የሚያከናውነው ብሔራዊ ቡድናችን ከዚህ ቀደም የመጨረሻውን ልምምዱን ከሚሰራበት መንገድ በተለየ መልኩ ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ቀለል ያለ እና ማጥቃትን መሰረት ያደረጉ ስራዎችን አከናውኖ ጨርሷል። ያም ቢሆን ጠዋት እንደ ቡድን ስብሰባ ማድረጋቸውን የሰማን ሲሆን በነገውም ጨዋታ አስቀድሞ ከተካሄዱት ሁለቱ ጨዋታዎች አሰልጣኝ ውበቱ ከተጠቀሙት የመጀመርያ አሰላለፍ መጠነኛ ለውጥ እንደሚኖርም ተጠብቋል።
ሽመልስ በቀለ ለብቻው ተነጥሎ በዛሬው ዕለት ቀለል ያሉ ልምምዶችን ሲሰራ ስንመለከት ግብጠባቂው ፋሲል ገ/ሚካኤል በአንፃሩ ከጉዳቱ በመጠኑም ቢሆን አገግሞ ልምምድ ሰርቷል። ከካሜሩኑ ጨዋታ በኃላ በነበረው የመጀመርያ ልምምድ ጉልበቱ ላይ የማበጥ ምልክት በማሳየቱ ልምምድ ያልሰራው አቡበከር ናስር በዛሬ የመጨረሻ ልምምድ ወቅት ከቡድን አጋሮቹ ጋር የተሟላ ስራ ሲሰራ ተመልክተናል። ይህን ተከትሎ አበቡበከር ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑን ቢታወቅም ነገ የመሰለፉ ጉዳይ በአሰልጣኙ የሚወሰን ይሆናል።
በተያያዘ የቡድኑ አባላት የኮቪድ ምርመራ አድርገው ሁሉም ነፃ መሆናቸው ታውቋል። ከዚህ ውጭ በቡድኑ ውስጥ የተለየ ነገር የሌለ ሲሆን ነገ ምሽት አንድ ሰዓት በሌሎች ቡድኖች ውጤት ላይ የተመሰረተውን ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ ዕድል ለመጠቀም ከቡርኪና ፋሶ ጋር ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።