“…በእጃችን ባለው ጨዋታ የምንችለውን ሁሉ አድርገን ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ያለችውን እንጥፍጣፊ ዕድል ለመጠቀም ዝግጁ ነን” አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

👉 “ከአዕምሯዊ ጥንካሬ አንፃር ለትልልቅ ጨዋታዎች የመዘጋጀት ነገራችን መጨመር አለበት”

👉 “ጎሉን ተዉትና ሌላው ያለን ነገር ላይ እናተኩር ብለን ወደራሳቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ነው የሞከርነው።”

👉 “የተለጠጠ እና የተጋነነ ነገር ነበር ያቀድነው የሚል ሀሳብ የሚያስነሳ ነገር የለም።”

👉 “ከቅያሪ ጋር ተያይዞ መዘግየቶች ነበሩ። እነሱም ደግሞ ክፋታቸው እስከምንቀይርም አልጠበቁንም።”

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከነገው ወሳኝ ጨዋታ በፊት ከምሽት 04:00 ጀምሮ ከሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ጋር ተከታዩን ሰፊ ቆይታ አድርገዋል።

የ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች በካሜሩን የተለያዩ ስታዲየሞች መካሄዳቸውን ቀጥለዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም እስካሁን ሁለት የምድብ ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን ሦስተኛውን እና የውድድሩ የመጨረሻ ዕጣ ፈንታውን የሚለየውን ጨዋታ ነገ ለማድረግ እየተዘጋጀ ይገኛል። ዛሬ ማምሻውን ይህንን ጨዋታ እና ያለፉትን ሽንፈቶች አስመልክቶ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከሀገር ውስጥ የሚዲያ ባለሙያዎች ጋር በበይነመረብ በመታገዝ ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

በቅድሚያ አሰልጣኙ ስለእስካሁኑ ጉዞ እና ቀጣዩ ጨዋታ ጠቅለል ያለ ሀሳባቸውን እንዲህ አጋርተዋል።

“ከኬፕ ቬርድ እና ከካሜሩን ጋር ያደረግናቸውን ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻልንም። የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ከበርኩና ፋሶ ጋር በነገው ዕለት እናደርጋለን። ሁለት ጨዋታ መሸነፋችን ወደ ቀጠዩ ዙር የማለፍ ዕድላችንን እንዳጠበበው ግልፅ ነው። ያም ቢሆን ግን መከፈል የሚቻለውን መስዕዋትነት በመክፈል ጨዋታውን አሸንፈን የሚመጣውን ዕድል ለመጠቀም በሙሉ ዝግጅት ላይ ነው ያለነው። ከካሜሩን ጨዋታ መልስ መጠነኛ ተጫዋቾች ላይ የነበረ የመንፈስ አለመረጋጋት እንደነበር አይተናል። ከዛ ቶሎ እንዲመለሱ እና የመጨረሻዉም ጨዋታ ወደ ቀጣይ ዙር ሊያሳልፈን እንደሚችል በመወያየት በጥሩ የቡድን መንፈስ ላይ እንገኛለን። በካሜሩኑ ጨዋታ በሀሉም ረገድ ከኬፕ ቬርድ ጋር ባደረግነው ጨዋታ ረጅም ሰዓት በጎዶሎ በመጫወታችን መጠነኛ ድካም ሊፈጠር እንደሚችል ግምቱ ነበረን። ያንን ሊቀንስ የሚችል የሪከቨሪ ሥራዎችን በመስራት ብዙዎቹ በጥሩ ፎርም ነው ወደ ሜዳ የገቡት። ጨዋታው በተጀመረ ከአምስት ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ጎል ማግባት ችለናል። ይህ ለእኛ ጥሩ ሞራል የሚሆን ነበር። መልሶ ግን ብዙም ሳይቆይ ጎል አስተናግደናል። ጨዋታውን ካሜሩን ለማሸነፍ የተሻለ ዕድል እንደነበረው በእንቅስቃሴ አይተናል ፤ ጎሎቹም የሚገልፁት ነው። ያም ቢሆን ግን በጨዋታው አጋጣሚዎችን አለመጠቀማችንም የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንደነበረው ነው ያየሁት። ከዛ መለስ ለነገው ጨዋታ ተዘጋጅተናል። ዞሮ ዞሮ ያኛው አልፏል። ከፊታችን በእጃችን ባለው ጨዋታ የምንችለውን ሁሉ አድርገን ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ያለችውን እንጥፍጣፊ ዕድል ለመጠቀም ዝግጁ ነን። ከጤና ጋር ተያይዞ ሁሉም ተጫዋቾች ከኮቪድ ነፃ ናቸው። ከሽመልስ በቀለ ውጪ አብዛኞቹ ጥሩ ጤንነት ላይ ናቸው። ምንአልባት ከአቡበከር ጋር ተያይዞ መጠነኛ ጉዳት አለበት። ከጨዋታው ያርቀዋል የሚለውን ግን እርግጠኛ አይደለሁም።”

በመቀጠል ከጋዜጠኞት ለተነሱ ጥያቄዎች አሰልጣኙ ተከታዮቹን ምላሾች ሰጥተዋል።

ቡድኑ ላይ ስለታዩ አካላዊ እና አዕምሯዊ ድክመቶች

“ከአካላዊ እና አዕምሯዊ ጉዳዮች አንፃር ጨዋታው ውስጥ እስከመጨረሻው ከመቆየት ጋር ተያይዞ እኔ ያየሁት ሁለተኛውን ነው።  ጨዋታው ከእጃችን በወጣበት ሰዓት ላይ ያንን ተሸክሞ ወደሚቀጥለው ነገር መውጣት የሚያስችል የአዕምሮ ደረጃ ላይ እንዳልነበርን ነው ያየሁት። በተለይ ሁለተኛው እና ሦስተኛው ጎል ሲገባ ብዙ ተጫዋቾች አካላዊ ቋንቋቸው ላይ የሚታይ ነገር ነበር። ከ1-0 3-1 መመራታችንን ዳገት አደርጎ የመውሰድ እና ያንን የመቋቋም አቅም እና ልምድ እንዳልነበረን ነው ያየሁት። በአካል ብቃት ደክመው ነበር ማለት የማልችልባቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ መስዑድ የመጀመሪያውን አጋማሽ ወደ ስድስት ኪሎሜትር ገደማ ነው የሸፈነው። ከ800 ሜትር በላይ በፈጣን ሩጫ የሄደባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ይሄን ይሄን ስንመለከት እና ጎሎቹ በገቡበት ሰዓት ራሱ ሳጥናችን ላይ የተመለሱ ተጫዋቾችን ቁጥር ስንመለከት ‘በአካል ደክመው ነበር’ ለማለት አላሳመነኝም። በአዕምሮ ግን ትክክል ነው። ከግቦቹ ነፊት በዳዋ ሆቴሳም የግብ ዕድል ፈጥረን ነበር። እነዛን ነገሮች ካየን ከአዕምሯዊ ጥንካሬ አንፃር ለትልልቅ ጨዋታዎች የመዘጋጀት ነገራችን መጨመር አለበት። በጨዋታ ላይ እንዲህ ዓይነት ነገር ይገጥማል።  በእኛ ደረጃ ያለ ቡድን ስለገጠመው ነው እንጂ በየትኛውም ሀገር ጨዋታ የተወሰኑ ደቂቃዎች ከእጅ ያመልጣሉ። ጎሎች ሲገቡ ተስፋ የመቁረጥ እና የማቀርቀር ነገር ነበር የሚታየው። ማግባት እንችላለን ብሎ ከጎል ውስጥ ኳስ ይዞ ወጥቶ መሀል ሜዳ ላይ የመጀመር ጠንካራ የአዕምሮ ደረጃ ላይ አልደረስንም። በዚህ ረገድ በደንብ ልምዱ ያስፈልገናል ነው የምለው።”

ተጫዋቾች ጫና ፈጥረው እንዲጫወቱ መልዕክት ስለማስተላለፋቸው

“እንደጨዋታ ዕቅድ ይዘነው የገባነው ነገር በተለይ የመጀመሪያው አጋማሽ ከዛም አልፎ ሦስተኛው ግብ እስኪቆጠርብን ድረስ በደንብ ሰርቷል ብዬ ነው የማስበው። አቡበከርን ፊት አድርገን 4-3-3 እንጫወት እንጂ 4-6-0 ሁሉ እንዲሆን አቡበከር ወደ መሀል ወርዶ እንዲጫወት እና እሱ የፈጠረውን ክፍተት ዳዋ እና አማኑኤል እንዲጠቀሙበት ነበር ያሰብነው። ያንንም በተግባር ጨዋታው ላይ አይተነዋል። በዛ መንገድ አግኝተናቸዋል። ዕድሎችን መፍጠር ፣ ክፍተቶችን ማግኘት እና ኳሱን በተመጣጠነ ሁኔታ መቆጣጠር ችለናል። የተወሰኑ ቅፅበቶች ላይ ግን ባልተመቸ ሁኔታ ላይ እዛው ተጭነው ኳስን መንጠቅ የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች እንዲፈጥሩም ነበር። በአንድ ሁለት አጋጣሚዎች ይህንን በማድረጋችን ኦናና ኳስ ወደ ውጪ አውጥቷል። አንዳንዴ እነዚህ ቅፅበቶች የሚገኙበትን አጋጣሚ የመርሳት ነገር ሲኖር ነው ያንን ለማስታወስ እንዲጫኑ ስናገር የነበረው እንጂ ዘጠና ደቂቃውን በሙሉ እንደካሜሩን ዓይነት ቡድን ጋር በከፍተኛ ጫና እንጫወታለን የሚል ዕብደት ውስጥ የለም።”

የአቡበከር ወደ ኋላ መሳብ ከፊት የዘጠኝ ቁጥርን ጥቅም ስለማሳጣቱ

“ሙሉ ለሙሉ አጥተናል ብሎ መደምደም ይከብዳል። ንፁህ ዘጠኝ ቁጥር እዛ ጋር ማስቀመጠም ጥቅም ይኖረዋል ብዬ አላስብም። በዛ መልክ የተጫወትንባቸው ጨዋታዎች ጥቂት ናቸው። በእርግጥ ዘጠኝ ቁጥሮቹን ራሱ ተጨማሪ ሌላ ሚና እየሰጠናቸው ነው የሚጫወቱት። አንዳንዴ እዛው እንዲቆዩ የምንፈልግበት ጊዜ አለ። በመጫወት ሳይሆን የተጋጣሚን ተከላካይ እዛው እንዲያቆዩልን እና መሀል ላይ ኳስ የማንሸራሸሪያ በቂ ክፍተት ለመፍጠር ማለት ነው። በዛ ጨዋታም ዳዋ እና አማኑኤል እንደዛ ዓይነት ኳሶችን አግኝተዋል። ምንአልባት በተመሳሳይ ከአማካይ ክፍል የሚሄዱ ተጫዋቾችን መፍጠር ላይ ገና ነው። መስዑድም ሆነ ሱራፌል በብዛት ወደ ታች ወረድ ብለው ኳስ የማመቻቸት ነገሩ ላይ ነው እያየናቸው ያለነው። በተረፈ ግን ሁለቱ እኔ በደንብ ተግብረውታል ብዬ ነው የማስበው። እንደውም በዚህ ደረጃ ከትልቅ ቡድን ጋር እየተጫወቱ እንዲህ ዓይነቱን ነገር መሞከራቸው ራሱ ትልቅ ነገር ነው። ሁለት ሦስት ዕድሎችን አግኝተናል። ከኳስ ውጪ ያለው ነገር ላይ ግን ክፍተት ነበር። በተለይ በእነሱ በኩል ከመስመር ተከላካይ ቦታ የሚነሱ እና ሀሰተኛ ሩጫ የሚሮጡ ፣ የመስመር ተጫዋቾቻችው ወደ ውስጥ ገብተው የእኛን መስመር ተከላካዮች ወደ ውስጥ አስገብተው ያንን ቦታ ለራሳቸው የመስመር ተከላካዮች የሚተዉበት ፣ ረጃጅም ኳሶችን የሚገለብጡባቸውን አጋጣሚዎች በደንብ ቀደመን አይተነዋል። ተነጋግረናል ለመስራትም ሞክረናል። ግን ደግሞ አተገባበሩ ላይ ክፍተቶች ነበሩብን። የቡድናችን ትልቁም ክፍተት የነበረው ያ ነው። በማጥቃቱ መጥፎ አልነበርንም። በመከላከሉ ግን ብዙ ዕድሎችን ፈጥረንላቸዋል።”

በዕረፍት እና ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ስለነበረው የቡድኑ ስሜት

“ዕረፍት ላይ የሁላችንም ስሜት አዎንታዊ ነው የነበረው። ተጨማሪ ጎል ልናገባ የምንችልበትን አጋጣሚ መፍጠር እንደምንችል ስሜቱ ነበረን። ያ እንደሚቻል ነው የነገርናቸው። ሁለተኛው ነገር በመጀመሪያው አጋማሽ ጎሎች አያግቡብን እንጂ የሰጠናቸው ሥራዎችን በአግባቡ እየተገበሩ እንዳልሆነ አይተነዋል። በመጠኑም ደግሞ ኳሶችን ለመመስረት ስንሞክር ከራሳችን ሜዳ ለመውጣት ስንሞከር ከእነሱ አጥቂ አንዱ ወረድ ብሎ አማኑኤልን ይሸፍን ነበር። አማኑኤል ራሱን ነፃ ሊያደርግ የሚችልባቸውን አንዳንድ ነገሮች ነው የተነጋገርነው። በተረፈ ከመስመር የሚመጡትን ማቆም ከቻልን የካሜሩንን የማጥቂያ መንገዶች በቁጥር የሚታዩ ሁለት እና ሦስት ዓይነት እንደሆኑ ነው ለመነጋገር የሞከርነው። ተጫዋቾችም ጥሩ ሞራል ላይ ነው የነበሩት። መጨረሻ ላይ ያው ከመምራት ተነስተህ በዛ መጠን ተሸንፈህ ስተወጣ የሚሰማህ ስሜት ይኖራል። የያዝከውን ነገር መጠራጠር ፣ ‘አንችልም’ ብሎ የማሰብ ዓይነት ነገር አይቻለሁ። ግን ያ እንዳልሆነ እና እንዲረጋጉ ለማድረግ ነው የሞከርነው። ዕውነታውም ያ ነው። በተለይ ደግሞ ተመልሰን ካየነው ዕድለኛም አይደለንም በውድድሩ። VAR ተግባራዊ ሆኗል። እኛ ላይ ነው በአብዛኛው ተግባራዊ የሆነው ማለት ይቻላል። በሁለት ጨዋታ ሦስት በVAR መታየት የሚገባቸው ነገሮች ተፈጥረዋል። ለምሳሌ ያሬድ ሲወጣ ዳኛውን ጠርተው በግድ እይ ብለው ደግመው ደግመው ደግመው በቀይ እንዲወጣ ነው የሆነው። እኛ ላይ የተቆጠረውም ግን የኳሱ መነሻ ከጨዋታ ውጪ ነበር። የVAR ጥቅሙ ደግሞ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎችን አይቶ ጎል በትክክል መቆጠሩን ማረጋገጥ ነው። ትልቅ ቡድን ብንሆን ምናልባት ይህ ነገር ሊታይ ይችል ነበር። መስዑድ ላይ ጥፋት ተሰርቶ የተቆጠረውም እንደዛው ፤ ያለመቻል አይደለም። ትክክለኛ ውሳኔ ቢወሰን እና ጎሉ ባይቆጠር ጨዋታው በዛ ያለመቀጠል ዕድሉ ሰፊ ነበር። ጎሉን ተዉትና ሌላው ያለን ነገር ላይ እናተኩር ብለን ወደራሳቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ነው የሞከርነው። ሁለት የተለያየ ጫፍ የነበረ ስሜት ነው የነበረው።”

በካሜሩኑ ጨዋታ ጌታነህ ስላልተሰለፈበት ምክንያት

ጌታነህ ጉዳት የለበትም ፤ በዛም አይደለም የተቀመጠው። ግን ማታ ማታ ላይ እንደ ሳይነስ ነገር ማፈን ነገር ነበረው። ያንን ነው እንደ ምክንያት ያየነው። እንጂ የተለየ ጉዳት ምናምን የለውም። 

ቡድኑ ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ያስቀመጠው ዕቅድ ባይሳካ…?

የተለጠጠ እና የተጋነነ ነገር ነበር ያቀድነው የሚል ሀሳብ የሚያስነሳ ነገር የለም። ከኬፕ ቨርድ ጋር የነበረው ጨዋታ ግን ይዘን የመጣነውን ዕድቅ ሙሉ ለሙሉ እንዳበላሸው ነው የገባኝ። በተለይ በጊዜ መሆኑ። የጨዋታ መንገዳችንን ከኋላ ይዞ ይሄዳል ብለን የምናስበውን ተጫዋች ነበር ያጣነው። በዛ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ለሁለተኛውም ጨዋታ የተሻገረ ነበር። ከካሜሩን ጋር ስንጫወት ወዴት መንገድ እንድንጫወት ያስገድዱን እንደነበር አይታችኋል። በተለይ ኳስ በአስቻለው በኩል እንዳይወጣ ያስገድዱን እና በምኞት ጋር ብቻ እንድንወጣ ከዛ እዛ ጋር ደግሞ ወጥመድ ውስጥ አስገብተውን ለመንጠቅ ይሞክሩ ነበር። ምኞት በርካታ ኳስ ነክቷል። ከነካቸው ኳሶች ስንቶቹ ውጤታማ ሆኑ ካልን ደግሞ የያሬድ ከዛ ጋር መጉደል የፈጠረው ተፅዕኖ እንዳለው ይሰማኛል። ይህ ቢሆን ኖሮ ከሁለቱ ጨዋታ የሆነ ነገር ይዞ መውጣት እንችል ነበር። ዕድላችን ገና አላለቀም። ያለውን ነገር እንሞክራለን። አዘጋጇ ካሜሩን ቀላል ቡድን አይደለችም። የትኛውም ቡድን ሊሸነፍ ይችላል። ግን ደግሞ በርካታ አዎንታዊ ነገሮች ነበሩ። አሁን የኢትዮጵያ ቡድን እዚህ መጥቷል። በቀጣይ ደግሞ በተደጋጋሚ መሳተፍ አለብን። ተጫዋቾቹም ይሄንን አይተውታል። ብዙ ወጣቶችም ስላሉ ተመልሶ መምጣት የማይቻልበት ምክንያት የለም። ይህ ማለት የነገው ጨዋታ አልቋል ማለት አደለም። የነገው ጨዋታ ቢኖርም ባይኖርም መመለሻችን ማጠር እንዳለበት ይሰማኛል። መሰራት ያለባቸው ነገሮች መሰራት አለባቸው። ሊጉን በአንድ ጊዜ ማሳደግ አንችልም። ቢያንስ እዚህ መጥተው ያዩ ተጫዋቾች ለሌሎች ማካፈል አለባቸው። ራሳቸውም ለቀጣዮቹ ውድድሮች ማዘጋጀት አለባቸው። ይሄ የመጨረሻችን የአፍሪካ ዋንጫ መሆን የለበትም።”

ስለሚያስቆጫቸው ነገር

“በራሴ ማድረግ እየቻልኩ ብዬ ያሰብኩት ነገር በካሜሩኑ ጨዋታ የመስመር ተከላካዮች ላይ የነበረውን ጫና መቀነስ የምችልበት ዕድል ነበረኝ። ከቅያሪ ጋር ተያይዞ መዘግየቶች ነበሩ። እነሱም ደግሞ ክፋታቸው እስከምንቀይርም አልጠበቁንም። እርግጥ ተጫዋቾቹ እያሟሟቁ ቢሆንም ከመግባታቸው በፊት ጎሎቹ ገብተው ጨዋታው ከእጃችን አመለጠ። ይሄ ይቆጨኛል።” 

ስለ ነገው ጨዋታ

“ጨዋታው አላለቀም። አንዳንድ ጊዜ አልቋል የሚል ስሜት ይሰማናል። በተለይ በሰፊ ጎል ከመሸነፋችን አንፃር። ቡርኪና ፋሶን ልናሸንፍ አንችልም የሚል መንፈስ ሰው ላይ ሊኖር ይችላል። ተጫዋቾቹም ጋር ሊኖር ይችላል። የሰው ችግር የለውም። እኛ ግን እንደባለሙያ ማድረግ ይቻላል ፤ ገና ነው። እናሸንፋለን ማለት እናልፋለን ማለት አይደለም። ከዛ በኋላ የሚመጡ ነገሮችን አናቅም። ጀብደኛ ሆነን ቡርኪና ፋሶን በዚህ ጎል እናሸንፋለን ብለን ቀድመን መናገር አንችልም። አይደለም እኛ የትኛውም ቡድን አይናገርም። እኛም ይሄንን ለማለት አቅሙም ሆነ ዝግጅቱ አለን ብዬ መናገር አልችልም። አሰላለፍ ላይ መጠነኛ ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ። በተለይ ከተጋጣሚ ቡድን ጋር ተያይዞ ያየናቸው ነገሮች አሉ። እኛ ላይ ብቻ ትኩረት ከምናደርግ የእነሱን ጨዋታ ስላጠናን ከዛ መነሻነት መጠነኛ ለውጥ ይኖራል ብዬ አስባለው። ሁለተኛም ሆነ ሦስተኛ ሆነን ለማለፍ እና ዕድላችንን ለመጠበቅ ማሸነፍ ያስፈልገናል። በጎል ረገድ ይሄን ያህል ይጠበቅብናል ብሎ ለተጫዋቾቹ መናገር በተወሰነ መልኩ ሊያነሳሳቸው ይችላል። በሌላ መልኩ ደግሞ ጫናም ሊፈጥር ይችላል። ስለዚህ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ዋናው ትኩረታችን ከማሸነፍ ጋር የተያያዘ ነው።”