ዋልያው በምድብ የመጨረሻ ጨዋታው አንድ ነጥብ ቢያገኝም ከውድድሩ ተሰናብቷል

ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ያለውን ጭላንጭል ተስፋ ለመጠቀም የምድብ ሦስተኛ ጨዋታውን ከቡርኪና ፋሶ ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንድ አቻ ቢለያይም ዕድሉን አምክኖ ከአፍሪካ ዋንጫው የተሰናበተ የመጀመሪያው ቡድን ሆኗል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከካሜሩን ጋር የምድብ ሁለተኛ ጨዋታቸውን አድርገው አራት ለአንድ ከተረቱበት ጨዋታ አራት ለውጦችን አድርገው ወሳኙን ጨዋታ ቀርበዋል። በዚህም በመጀመሪያው ጨዋታ ቀይ ካርድ አይቶ አንድ ጨዋታ አምልጦት የነበረው ያሬድ ባየህ ምኞት ደበበን፣ ይሁን እንዳሻው መስዑድ መሐመድን፣ አስራት ቱንጆ ሱሌይማን ሀሚድን እንዲሁም ጌታነህ ከበደ አማኑኤል ገብረሚካኤልን ተክተው የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ገብተዋል።

ተመጣጣኝ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች መሐል ሜዳ ላይ የተገደበ እና ኳስን ቶሎ ቶሎ መነጣጠቅ የታየበት ነበር። በጨዋታው ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ጥቃት ፈፅሟል። በ9ኛው ደቂቃም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በግራ መስመር የተገኘን የመዓዘን ምት በቶሎ በመጀመር ለመጠቀም ዳዋ ቢጥርም ተከላካዮች አውጥተውበታል።

ከሰከንዶች በኋላ ደግሞ በተቃራኒ መስመር ሌላ የመዓዘን ምት ተገኝቶ ወደ ሳጥን የተሻማው ኳስ በተከላካዮች ሲመለስ ረመዳን እና አቡበከር ተቀባብለው ጌታነህ የመጨረሻ ኳስ አሽኝቶ ወደ ግብ ቢመታውም የግብ ዘቡ ፋሪድ ኦድሮጎ በጥሩ ቅልጥፍና አድኖታል። ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስሉት ቡርኪና ፋሶዎች እጅግ ወርቃማ ዕድል አግኝተው ነበር። በዚህም ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ የመሐል ተከላካዩ ያሬድ ለማውጣት ባደረገው ጥረት ስህተት ፈፅሞ ቡርኪናዎች ዕድል አግኝተው ነበር። ነገርግን ዕድሉም መጠቀም ሳይችሉ ተመልሰዋል።

ወደ ግብ በመድረስ እና ኳስን በመቆጣጠሩ ረገድ በአንፃራዊነት የተሻሉት ዋልያዎቹ በ23ኛው ደቂቃ ዳዋ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ ቀዳሚ ሊሆኑ ነበር። ይህ ሙከራ ከተሰነዘረ ከደቂቃ በኋላ ግን ቡርኪና ፋሶዎች ወደ መሪነት የተሸጋገሩበትን ጎል አግኝተዋል። በዚህም አዳማ ጎይራ ከመሐል የላከውን ተንጠልጣይ ኳስ በአስራት እና አስቻለው መሐል አፈትልኮ የወጣው ባሮስ ባያላ የግብ ጠባቂው ተክለማርያምን ግቡን ለቆ መውጣት ተከትሎ በዐየር ላይ በመላክ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ምላሽ ለመስጠት ከጫፍ የደረሱ የመሰሉት የአሠልጣኝ ውበቱ ተጫዋቾች በጊዜው የፈጠሩትን አጋጣሚ በጌታነህ አማካኝነት ለመጠቀም ቢሞክሩም ግብ ጠባቂው አምክኖባቸዋል። በቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ሙከራ ሳይስተናግድ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

የሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ አቡበከር ናስር ላይ ጥፋት ተሰርቶ የተገኘውን የቅጣት ምት ሱራፌል ሲያሻማው ኳስ በእጅ ተነክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፍፁም ቅጣት ምት አግኝቷል። በቪ ኤ አራ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምትም የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ በ52ኛው ደቂቃ ወደ ግብነት ቀይሮታል። የአቻነት ግብ ከተቆጠረ በኋላ እድገት ያሳዩት ቡርኪናዎች ዳግም ወደ መሪነት ለመመለስ ፍጥነት የታከለበት አጨዋወት መከተል ይዘዋል። በተለይ በ64ናው ደቂቃ ፋይሳል ኦታራ በመስመሮች መካከል ከትራዎሬ የተቀበለውን ኳስ አክርሮ መትቶ የፈጠረው ዕድል አስደንጋጭ ነበር።

አሁንም ኳስን ተቆጣጥረው መጫወት የቀጠሉት ዋልያዎቹ አማካይ እና የመስመር አጥቂ ለውጠው በማስገባት ሦስት ነጥብ ለማግኘት ጥረዋል። ከቅያሪዎቹ መካከል አንዱ የሆነው መስፍን ታፈሰ ደግሞ በ69ኛው ከወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ አክርሮ የመታ ቢሆንም ኳሱ ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። በመጨረሻዎቹ የጨዋታው ደቂቃዎችም ዋልያው በተሻለ ወደ ተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ እየደረሰ ግብ ፍለጋ ቢቀጥልም የመጨረሻው የማጥቃት ሲሶ ላይ መጣደፎች እና ችኮላዎች እየተስተዋሉ ፍሬያማ መሆን አልተቻለም። ጨዋታውም ሌላ ግብ ሳይስተናገድበት አንድ አቻ ተጠናቋል። የዋልያዎቹ አማካይ አማኑኤል ዮሐንስም የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።

በዚሁ ምድብ የሚገኙት ካሜሩን እና ኬፕ ቨርድም በተመሳሳይ ጨዋታቸውን አንድ አቻ አገባደዋል። ውጤቶቹን ተከትሎም የውድድሩ አዘጋጅ ካሜሩን በ7 ቡርኪና ፋሶ ደግሞ በ4 ነጥቦች በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፉ ሲያልፉ እንደ ቡርኪና አራት ነጥብ ያላት ኬፕ ቨርድ ደግሞ ምርጥ ሦስተኛ ሆኖ ለማለፍ ያላትን ዕድሏን አስፍታለች። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ በአንድ ነጥብ እና በአራት የግብ ዕዳ የምድቡ የመጨረሻ ደረጃን ይዞ ከውድድሩ ተሰናብቷል።