​አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከጨዋታው በኋላ አስተያየት ሰጥተዋል

👉”በዚህ ውድድር ያገኘነው ዋናው ነገር ልምድ ነው”
👉”ለወደፊቱ በትክክለኛው መንገድ ላይ መሆናችንን አምናለሁ”
👉”…ተጫዋቾቻን በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የዳኞች ውሳኔ ሲዛባ አቤቱታ ለማቅረብ አይናፋር…”
👉”በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ እንመለሳለ የሚል እምነት አለኝ”

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከሚሳተፉ 24 ቡድኖች መካከል አንዱ እንደነበር ይታወቃል። ቡድኑም በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ካሜሩን፣ ኬፕ ቨርድ እና ቡርኪና ፋሶ ጋር ተደልድሎ ሦስት ጨዋታዎችን በስምንት ቀናት ልዩነት ያከናወነ ሲሆን አንድ ነጥብ በመያዝም ከውድድሩ የተሰናበተ የመጀመሪያው ቡድን ሆኗል። የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተም ከቡርኪና ፋሶ ጋር ቡድናቸው አንድ አቻ ከተለያየ በኋላ ስለጨዋታው እና አጠቃላይ የአፍሪካ ዋንጫ ቆይታቸው ከብዙሃን መገናኛ አባላት ጋር ቆይታ አድርገዋል። በቅድሚያም አሠልጣኙ ተከታዩን ገለፃ ሰጥተዋል።


“ከውድድሩ ተሰናብተናል። ምክንያቱም ጨዋታዎችን ማሸነፍ ስላልቻልን። ከመጀመሪያው የኬፕ ቨርድ ጨዋታ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ምን አይነት መልክ እንዳለን እና ቀለማችንን ለማሳየት ሞክረናል። ግን ደግሞ ከኬፕ ቨርድ ጨዋታ ጀምሮ ነገሮች ከቁጥጥራችን ውጪ እየሆኑ ነበር። የሆነው ሆኖ ዛሬ ማሸነፍ አልቻልንም። እርግጥ ብናሸንፍም ወደ ጥሎ ማለፉ ለማለፍ በቂ አልነበረም። በእንቅስቃሴ ግን ጨዋታውን ለመቆጣጠር እና የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረናል። አንድ ግብም ቢያንስ አስቆጥረናል። እንዳልኩት ግን ለማለፍ ይህ በቂ አልነበረም። በአጠቃላይ ብዙ ነገሮችን ተምረናል። ብዙ ወጣት ተጫዋቾች አሉን። እነዚህ ወጣት ተጫዋቾች ደግሞ ልምድ እያገኙ ሲሄዱ ጥሩ ነገር ይፈጠራል። በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ እንመለሳለ የሚል እምነትም አለኝ።” የሚል ሀሳባቸውን ካጋሩ በኋላ በስፍራው የተገኙ ጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበውላቸዋል።

ከውድድሩ ስለተማሩት ነገር?

እንደምታውቁት አብዛኞቹ ተጫዋቾች በሀገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ናቸው። በእንደዚህ አይነት ውድድሮች የተሻሉ ደረጃዎችን ለመጓዝ ልምድ ያስፈልጋል። ይህ ልምድ ደግሞ በአንድ ጀንበር አይገኝም። ስለዚህ ጨዋታዎችን በማድረግ የተሻሉ ተጫዋቾች እንዲኖረን ማድረግ አለብን። በዚህ ውድድርም ያገኘነው ዋናው ነገር ልምድ ነው። በአንዳንድ መመዘኛዎች ደካሞች ነበርን። እነዛ ላይም መስራት ይጠበቅብናል። 

በውድድሩ ቆይታቸው ስለሚቆጫቸው ነገር?

የሚቆጨኝ በተለይ በካሜሩኑ ጨዋታ ተጫዋቾቻን በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የዳኞች ውሳኔ ሲዛባ አቤቱታ ለማቅረብ አይናፋር መሆናቸው ነው። የካሜሩኑን ጨዋታ በድጋሚ ብትመለከቱ የመጀመሪያው ግብ መሉ ለሙሉ ከጨዋታ ውጪ ነበር። በእርግጥ ለተጫዋቾቹም ሆነ ለእኔ ከዕይታ ውጪ ነበር ፤ በኋላ ላይ ምስሉን ተመልክቼ ነው የተረዳሁት። ሦስተኛው ጎልም አምበላችን ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘ ነው። ከዛ አንፃር 4-1 መሸነፍ አይገባንም ነበር። ከዚህ በተጨማሪ የነበሩ ድክመቶችን ለማረም ቅያሬዎችን ለማድረግ ዘግይቼ ነበር። ቅያሬዎችን ከማድረጌ በፊት ሁለት ግቦች በሁለት ደቂቃዎች ተቆጥረው ጨዋታው ከእጃቸው ወጥቷል። ይህ ለእኛ ትምህርት የሚሆን ነው። በእግርኳስ እነዚህ የሚያጋጥሙ ነገሮች ናቸው ።


ከውድድሩ ስላገኙት ልምድ?

የውድድሩ ምድብ ድልድል ሲወጣ ከካሜሩን ፣ ኬፕ ቬርድ እና በርኪና ፋሶ ጋር ሲደርሰን ምናልባትም ከእኛ በሁለት ዕጥፍ የራቀ የእግርኳስ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ እንገነዘብ ነበር። እኛም ያለንን ነገር በማሳየት ልዩነቱን ማጥበብ እንደሚቻል ለማሳየት ሞክረናል። በቀጣይ እግርኳሳችንን በሂደት ለማሻሻል እንሞክራለን። ለወደፊቱ በትክክለኛው መንገድ ላይ መሆናችንን አምናለሁ። የጀመርነውን ነገር ለማስቀጠል ጠንክረን ከሰራን ከሌሌች ጋር ያለንን ልዩነት ማጥበብ እንችላለን። 

ስለበርኩና ፋሶ ቡድን?

በመጀመሪያ ወደ ቀጣዩ ዙር ስላለፉ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ጥሩ ቡድን አላቸው ፤ እኛ በተቻለን መጠን ልንፈትናቸው ሞክረናል። በቀጣይ ጨዋታዎች ገፍተው እንደሚሄዱ ተስፋ አደርጋለሁ።