​በወሳኙ የግብፅ እና ሱዳን ፍልሚያ ላይ በዓምላክ ተሰማ በዳኝነት ይሳተፋል

ነገ ምሽት አራት ሰዓት በሚደረገው ተጠባቂው የግብፅ እና ሱዳን ፍልሚያ ላይ ኢትዮጵያዊው ዳኛ በዓምላክ ተሰማ በዳኝነት እንደሚሳተፍ ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

በካሜሩን አስተናጋጅነት እየተከናወነ የሚገኘው የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ ውድድር ከትናንት ጀምሮ የምድብ ሦስተኛ እና የመጨረሻ ጨዋታዎችን ማከናወን እንደጀመረ ይታወቃል። እነዚሁ የምድብ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ሲቀጥሉም በምድብ አራት ደግሞ የመጨረሻ ተጠባቂ ፍልሚያዎች ነገ በተመሳሳይ 4 ሰዓት ይከናወናሉ። በዚሁ ምድብ የምትገኘው ናይጄሪያ ቀድማ ወደ ጥሎ ማለፉ መግባቷን ብታረጋግጥም ግብፅ፣ ጊኒ ቢሳው እና ሱዳን ደግሞ ዕድላቸውን በመጨረሻው ጨዋታ የሚሞክሩ ይሆናል።

በተለይ ደግሞ በአህማዱ አሂጆ ስታዲየም የሚከናወነው የግብፅ እና ሱዳን ጨዋታ በትልቅ ጉጉት የሚጠበቅ ሲሆን ኢትዮጵያዊው ዳኛ በዓምላክ ተሰማም በዳኝነት እንደሚሳተፍ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በዚህም ጨዋታውን ቦትስዋናዊው የመሐል ዳኛ ጆሹዋ ቦንዶ ከአንጎላ እና ሲሸልስ ከመጡ የመስመር ረዳት ዳኞች እንዲሁም ከአንጎላዊው አራተኛ ዳኛ ጋር እንደሚመሩት ሲመላከት የቪ ኤ አር ቀዳሚ ዳኛ ደግሞ በዓምላክ ተሰማ ከሞሮኳዊው ረዳት የቫር ዳኛው ጋር እንዲሆኑ መመደባቸውን አውቀናል።

በዓምላክ ተሰማ ከአራት ቀናት በፊት ሴኔጋል እና ጊኒ ያደረጉትን እና ያለ ግብ አቻ የተለያዩበትን ጨዋታ በመሐል አልቢትርነት የመራ ሲሆን ቀደም ብሎ ደግሞ ነገ በሚመራው ምድብ የሚገኙት ናይጄሪያ እና ግብፅ ተጫውተው ናይጄሪያ ስታሸንፍ የቪ ኤ አር ቀዳሚው ዳኛ ሆኖ ነበር። ይህንን ተከትሎም በዓምላክ ግብፅን ለሁለተኛ ጊዜ በቪ ኤ አር ዳኝነት የሚዳኝ ይሆናል።