የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዱዋላ ደርሷል

ከ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በጊዜ ከውድድሩ ውጭ መሆኑን ትናንት ያረጋገጠው ብሔራዊ ቡድኑ ዱዋላ ከተማ ደርሷል።

ከምድቡ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዶ በአንዱ ነጥብ የተጋራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለቀናት ከተቀመጠበት ገጠራማዋ መንደር ባንጉ በመልቀቅ የአውሮፕላን ጉዞ በማድረግ የካሜሩን ሁለተኛ ከተማ የሆነችው ዱዋላ መድረሱ ተረጋግጧል። ዋልያዎቹ በዱዋላ ከተማ መድረሳቸው ይታወቅ እንጂ ወደ ሀገር ቤት መቼ እንደሚመለሱ እስካሁን ቁርጥ ያለ ቀን አልታወቀም። ምክንያቱም ወደ ኢትዮጵያ የሚሄዱ በራራዎች ውስን መሆናቸውን ተከትሎ ሲሆን የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ አመራሮች ብሔራዊ ቡድኑን እና ሌሎችንም አካላት ጨምሮ የፊታችን ሐሙስ አልያም ቅዳሜ እንዲሄዱ ጥረት እያደረጉ ይገኛል።


ሁኔታዎች በታሰበው መልኩ ከሄዱ ከላይ በጠቀስናቸው ቀናት ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ ያቀናል ተብሎ ሲጠበቅ ይህ ካልሆነ ግን በዱዋላ ከተማ ቆይታ እያደረገ በተገኘው የበረራ ቀን ወደ አዲስ አበባ የሚመለስ እንደሆነ ሰምተናል።