​የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የሚጀምርበት ቀን ታውቋል

ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር የተቋረጠው የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በድሬዳዋ ከተማ የ10ኛ ሳምንት ጨዋታዎቹን በቀጣይ ሳምንት ማከናወን ይጀምራል።

የ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት እና ውድድር የዘጠኝ ሳምንታት ጉዞን በሀዋሳ ከተማ አከናውኖ ታህሣሥ 15 መቋረጡ ይታወሳል። የሊጉ አስተዳዳሪ አካልም በጊዜያዊነት አፍሪካ ዋንጫው ከተጠናቀቀ ከአምስት ቀናት በኋላ ሊጉን ለመቀጠል አቅዶ የነበረ ቢሆንም ብሔራዊ ቡድናችን ገና በጊዜ ከምድቡ መሰናበቱን ተከትሎ የሊጉን የመጀመሪያ ቀን አጢኖ ውሳኔ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትናንት ምሽት ከካሜሩን ተነስቶ አዲስ አበባ መግባቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ክለቦች ተጫዋቾችን (በብሔራዊ ቡድን የሚገኙ) ማግኛ 7 ቀናት በመስጠት ጥር 20 (ዓርብ) ሊጉ በድሬዳዋ እንዲቀጥል መወሰኑን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። ከደቂቃዎች በፊትም 16ቱም ክለቦች የመጀመሪያውን ቀን በደብዳቤ እንዲያውቁ እንደተደረገ ተረድተናል።

ከሊጉ ጋር በተያያዘ ዜና በሀዋሳ የተደረጉት ጨዋታዎች በአዘቦት ቀን 9 እና 12 እንዲሁም ቅዳሜ እና እሁድ 8 እና 12 ሰዓት መጀመራቸው ይታወሳል። ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ በድሬዳዋ የሚደረጉት ጨዋታዎች ግን በከተማው ካለው ሙቀት መነሻነት የሰዓት ለውጥ ሊደረግባቸው እንደሚችል ሰምተናል። ከውድድሩ የቀጥታ ስርጭት ባለ መብት ዲ ኤስ ቲቪ ጋር አክሲዮን ማኅበሩ ንግግሮች እያደረገ እንደሆነ ያወቅን ሲሆን ምናልባት 10 እና 1 ሰዓት ጨዋታዎች ሊጀመሩ የሚችልበት ዕድልም እንዳለ ተጠቁሟል።