የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ባለክብሮቹ ለወሳኙ ጨዋታ ወደ ታንዛኒያ ከማምራታቸው በፊት የመጨረሻ ልምምዳቸውን ረፋድ ላይ ሰርተዋል
በኮስታሪካ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የዓለም ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ለመሳተፍ በአሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች የሩዋንዳ እና ቦትስዋና አቻውን በሰፊ የጎል ልዩነት በመርታት ለዋናው ውድድር እየተቃረበ እንደሆነ ይታወቃል። ከፊቱ ላሉበት ሁለት የ180 ደቂቃዎች ወሳኝ ጨዋታም ራሱን እያዘጋጀ የሚገኘው ቡድኑ በቅድሚያ ከታንዛኒያ ጋር ላለበት የደርሶ መልስ ጨዋታ ከጥር 2 ጀምሮ ማረፊያውን በካፍ የልዕቀት ማዕከል በማድረግ ሲዘጋጅ ነበር።
ልምምድ ሜዳ በማግኘቱ ረገድ የተቸገረ የሚመስለው ቡድኑ ማረፊያውን ባደረገው ማዕከል የሚገኘው የመጫወቻ ሜዳ ምቹ አለመሆኑን ተከትሎ ያለፉትን ቀናት በ35 ሜዳ፣ ጊዮርጊስ ሜዳ እና አበበ ቢቂላ ስታዲየም ልምምዱን ሲሰራ የነበረ ሲሆን በነገው ዕለት ወደ ታንዛኒያ ከማምራቱ በፊት የመጨረሻ ልምምዱን ረፋድ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው የጊዮርጊስ ሜዳ አከናውኗል።
ከ3:30 ጀምሮ መከናወን በጀመረው ልምምድ ላይ 25 ተጫዋቾች (21 ተጫዋቾች እና 4 የግብ ዘቦች) የተሳተፉ ሲሆን በተለያየ ምዕራፍ በተከፋፈሉ ሥራዎችም ለ2 ሰዓት የቆየ ልምምድ ሰርተዋል። በቅድሚያ ተጫዋቾቹ ሜዳውን በመዞር እንዲያሟሙቁ ከተደረገ በኋላ አራት አራት ሆነው መሀል ባልገባ ይዘት ያለው ጨዋታ ተጫውተው በደንብ እንዲያፍታቱ ተደርጓል። በመቀጠል የቡድኑ የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ ፀጋዘአብ አራቱን የግብ ዘቦች ለብቻ ነጥሎ የራሳቸውን ልምምድ ሲያሰራ ዋናው አሠልጣኝ ፍሬው እና ረዳቱ ምትኬ ደግሞ የሜዳ ላይ ተጫዋቾቹን ፍጥነት፣ ቅልጥፍና እና የአካል ብቃት ላይ ያተኮረ አራት አይነት ሥልጠና ሲሰጡ አስተውለናል።
ዘለግ ያለ ደቂቃ ከወሰደው ሥልጠና በኋላ ደግሞ አስራ ስድስት ከሀምሳው አካባቢ በፍጥነት እየተገኙ ኳሶችን ወደ ግብ የመምታት ልምምድ ሲሰራ ነበር። በድግግሞሽ ከተሰራው ይህ ልምምድ በኋላ ደግሞ የመከላከል ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች ኳሶችን በአንድ ንክኪ የሚያፀዱበትን ሂደት አሠልጣኝ ፍሬው ሲያሰሩ አይተናል። ልምምዱም 5:30 ሲል ሞቅ ባለው የተጫዋቾቹ ጭፈራ ታጅቦ ተቋጭቷል።
በመጀመሪያው የቡድኑ ጥሪ 28 ተጫዋቾች ተካተው የነበረ ሲሆን ከወቅታዊ ብቃት ጋር ተያይዞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተመረጡት ንግስት አስረስ እና ሰናይት ሼጎ፣ ከድሬዳዋ የተመረጠችው ባንቺይርጋ ተስፋዬ እና ከቦሌ የተመረጠችው ንጋት ጌታቸው እንደተቀነሱ አውቀናል። ከዚህ ውጪ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ የግብ ዘብ ቤቴልሄም ዮሐንስ እንደ አዲስ ጥሪ ቀርቦላት ስብስቡን መቀላቀሏን በቡድኑ የልምምድ መርሐ-ግብር ተገኝተን አረጋግጠናል።