ዋልያዎቹ አዲስ አበባ ደርሰዋል (ዝርዝር ዘገባ)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዱዋላ ከተማ በመነሳት ምሸት አዲስ አበባ ደርሷል። ይህን አስመልክቶም የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅረናል።

የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ቆይታው ከምድቡ ማለፍ ተስኖት ቆይታውን ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሁለት ምዕራፍ የተደረገውን በረራውን በማጠናቀቅ ማምሻውን አዲስ አበባ ደርሷል። ያውንዴ ከተማ የነበረው በአቶ ኢሳይያስ ጂራ የሚመራው የሥራ አስፈፃሚ አባላት እና ሌሎች አካላት ጨምሮ በቦይንግ 787 ከቀኑ 08:00 ከያውንዴ ከተማ በመነሳት ለ25 ደቂቃ በረራ የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ወደ ሚገኙበት ዱዋላ ከተማ ጉዞ አድርጓል።

ከያውንዴ ከተማ ከመነሳቱ አስቀድሞ የያውንዴ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወካይ በመሆን እና የኢትዮጵያ የልዑክ ቡድን በፍጥነት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ የማሳለጡን ስራ በአግባቡ ትከውን በነበረው ወ/ት ሄርሜላ አማካኝነት አሸኛኘት እና የፎቶ ፕሮግራም ተካሂዷል። በዚህ ጉዞ ውስጥ ሱዳን ብሔራዊ ቡድን አባላት የተካተቱ ሲሆን በአጋጣሚ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ስትመስ የመጨራሻውን ጨዋታ ሱዳንን በማሸነፍ ስታረጋግጥ የወቅቱ የሱዳን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና ዶ/ር መሐመድ ማዝዳ መገኘታቸው አጋጣሚውን አስገራሚ አድርጎታል።

ከ25 ደቂቃ በኋላ ዱዋላ ከተማ የደረሰው ቦይንግ 787 ለአንድ ሰዓት ቆይታ አድርጎ ለቀናት በዱዋላ ቆይታ የነበረው በአቶ አበበ ገላጋይ የሚመራው የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ወደ አውሮፕላኑ እንዲገቡ ተደርጓል። በዚህ ጉዞ ውስጥ ከሱዳን ብሔራዊ ቡድን በተጨማሪ የዚምባብዌ ብሔራዊ ቡድን አብረው በመካተት ወደ አዲስ አበበ ተጉዘዋል።

በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር አስር ሰዓት ተኩል ከዱዋላ ከተማ የተነሳው አውሮፕላን ከአራት ሰዓት በረራ በኃላ ምሽት ላይ አዲስ አበባ ዓለም ዓቀፍ ኤርፖርት ደርሷል። ኤርፖርት ሲደርስም የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ እና አቶ ኦሌሮ ኦፒዮ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣ አቶ ሰለሞን ገብረሥላሴ የፌዴሬሽኑ ምክትል ፀሐፊ እና ዶ/ር ወገኔ ዋ/ንጉስ የሊግ ካምፓኒው የውድድር ኮሚቴ ሰብሳቢ አበባ በመያዝ አቀባበል አድርገውላቸዋል። በማስከተል ከአዲስ አበባ ውጭ የሚኖሩ የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ወደ ጂፒተር ሆቴል ያቀኑ ሲሆን የቀሩት ወደ መኖርያ ቤታቸው አምርተዋል። በቀጣይ ቀናት ውስጥ የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የሚጀምር መሆኑን ተከትሎ ከተወሰኑ እረፍቶች በኋላ ክለቦቻቸውን የሚቀላቀሉ ይሆናል።

ሶከር ኢትዮጵያም ከያውንዴ እና ባፉሳም ከተማ ለአስር ቀናት ብሔራዊ ቡድኑን በተመለከተ በልዩ ዘገባዎቿ ወደ እናንተ ስታደርስ የቆየችውን መረጃ በዚሁ የምታጠናቅቅ ይሆናል።

ያጋሩ